ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 23, 2015

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 961፣ህዳር 14 እና ወጣት ትሑት ዘመድ (እውነተኛ ታሪክ ከማስታወሻ ደብተሬ)




ከጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ፣ኖርዌይ 

ሁሉን አክባሪው አቶ ሰለሞን 

ከትምህርት ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ የስራ ዓለምን የተቀላቀልኩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስርያቤትን ነበር።ለገሃር የሚገኘው ቴሌ አጠገብ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጭ ህንፃ አምስተኛ ፎቅ የሰው ኃይል አስተዳደር እና ቅጥር ክፍል ቢሮ በርን ቀስ ብዬ ቆረቆርኩት እና  ቀስ ብዬ ከፍቼ ወደ ውስጥ ዘለኩ።ምቹ በሆነ ሰፊ ወንበር ላይ ''አቶ ሰለሞን የሰው ኃይል አስተዳደር ክፍል ኃላፊ'' የሚል ፅሁፍ ጀርባ ትከሻው ሰፊ በስፖርት የዳበረ እና ንቁ ሰው ተቀምጧል።አቶ ሰለሞን።

''ይግቡ!'' አለና በሩን ከፍቼ ወደ ውስጥ ስገባ በመነፀሮቹ አናት ላይ ተመለከተኝ እና ከመቅፅበት ከመቀመጫው ተነሳ። በጣም ደነገጥኩ። ቀጠለና ''ጤናይስጥልኝ ምን ልርዳህ? ግባ ግባ'' አለና እጆቹን ዘረጋልኝ።በፍጥነት ጠጋ ብዬ የተዘረጉ እጆቹን ማክበሬን ለመግለጥ በግራ እጄም ጭምር ደግፌ ጨበጥኩት።ቀጠልኩ እና መናገር ስጀምርም አቶ ሰለሞን እንደቆመ ሲያናግረኝ ይበልጥ ትህትናው አስገረመኝ።በቀን ስንት ጊዜ ይነሳል? ሰው በገባ በወጣ ቁጥር እንዴት ይችለዋል? ብዬ ከእራሴ ጋር እየተሟገትኩ -

'' እ እ ደውላችሁልኝ ነበር።እዚህ መስርያቤት ለስራ'' ስለው ይበልጥ ፈገግ ብሎ እንድቀመጥ በእጁ በድጋሚ ወንበሩን አሳይቶኝ ከፊቱ ካለው ቀይ የወረቀት ትሪ ላይ አንድ ወረቀት አንስቶ እያየ 

''ስም ማን ልበል?'' አለኝ። ''ጌታቸው በቀለ'' አልኩት። አገኘው እና በእስክርብቶው ምልክት አደረገበት እና ቀና ብሎ በፈገግታ እያየኝ።''አቶ ጌታቸው የመስርያቤታችን ባልደረባ በመሆንህ ደስተኛ ነኝ'' አለና ወረቀቶች እየመረጠ በአንድ ክላሰር ላይ ካደረገ በኃላ  ''እነኝህን ፎርሞች  ትሞላለህ፣ይህንን ፖሊስ ጋር ወስደህ አሻራ ትሰጣለህ፣ይህንን ደግሞ ተያዥ ሥራ ላይ ያለ ሰው ታስፈርማለህ፣ይህንን ለሆስፒታል ምርመራ፣ይህ ላንተ ቀሪ'' እያለ ካሳየኝ በኃላ በመጪው ሳምንት ሁሉን ጨርሼ እንድመጣ ነግሮኝ እንደገና ከመቀመጫው ተነስቶ ከጨበጠኝ በኃላ ከክፍሉ ወጣሁ።

ከንግድ ባንክ ቢሮ እንደወጣሁ ቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የቀድሞ የክፍሌ ልጆች ጋር አምባሳደር ኬክ ቤት ጋር ተቀጣጥረን ስለነበር ወደዚያ አመራሁ።እዚያ እንደደረስኩ የክፍሌ ልጆች አምባሳደር ኬክ ቤት በር ላይ ቆመው ይጠብቁኝ ኖሮ ወደውስጥ ለመግባት ቦታ እንደሞላ እና ዋናው ፖስታ ቤት ስር የሚገኘው ''ራንዴቭኦ'' ካፍቴርያ ማምራት እንዳለብን ቀድመው መወሰናቸውን ነገሩኝ። ''ራንዴቭኦ'' በተለይ በውጭ በረንዳው በኩል ሰፊ በመሆኑ ለሰባታችንም በሰፊው ከበን ለመቀመጥ ተመቸን።ሁላችንም ከትምህርት ዓለም በኃላ ስለገባንበት መስርያቤት ማውራት ጀመርን።ልማት ባንክ የገቡት ወድያውኑ የሳምሶናይት ቦርሳ እንደተሰጣቸው እና ስልጠና መጀመራቸውን ኮራ እያሉ ሲነግሩን፣ የግል ድርጅት የገቡት ደግሞ ስለገንዘቡ ክፍያ የቀረነውን ማቁለጭለጭ ያዙ።ንግድ ባንክ የገባነው ደግሞ የንግድ ባንኩ የሰው ኃይል ኃላፊ የአቶ ሰለሞን ትሕትናን እያደነቅን ነገርናቸው።ንግድ ባንክ የገቡት  ለካ ሁሉም በልቡ የአቶ ሰለሞን ፍቅር የተላበሰ ትህትና እያወጣ እያወረደ ነበርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገና ሥራ ሳይንጀምር ወደድነው።በተለይ ሁለት የክፍላችን ልጆች ሥራ ባገኙበት መስሪያ ቤት የነበረውን የንቀት አስተያየት እያነሱ ሲነግሩን የኛውን ንግድ ባንክ ገና ሳንገባበት ሳሳንለት።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ እየሰሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አካል መሆን 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኞችን ሲቀጥር በቻለው መጠን ሰራተኞች በሚኖሩበት አካባቢ እንዲሆን ይጥራል።የስራ ምደባችን ሲደለደል ሁሉም በሚኖርበት ቀበሌ አካባቢ ሲመደብ የእኔዋ ሰፈር የወሎ ሰፈር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለሚቀርብ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ እንድመደብ ተወሰነ።

''አቶ ጌታቸው በቀለ ከፍተኛ ---ቀበሌ --- ማለት ወደ አይቤክስ ሆቴል የሚወስደው መንገድ ወሎ ስፈር ጥሩ እዚያጋ የባንካችን ሰርቪስ አለ አመቺ ይመስለኛል።ስለዚህ አቶ ጌታቸው ''ኤርፖርት ቅርንጫፍ'' ተመድበሃል'' አለኝ አቶ ሰለሞን የቅጥር ደብዳቤዬን ሲሰጠኝ እና ለቅርንጫፍ ሥራ አስያጅ የሚሰጠውን ደብዳቤ እያሳየኝ።ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የነበሩት ፒኮክ ሬስቱራንት እና አየር መንገድ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ነበር።የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ባንኩ በወቅቱ ብቸኛ የባንክ አገልግሎት ሰጪ ነበር።ማለትም ምንም የግል ባንኮች አልተከፈቱም።አየር መንገዱ ውስጥ የሚገኘው የተርሚናል አገልግሎት እና ግቢው ውስጥ ሁሉንም የባንክ አገልግሎት የሚሰጠው ''አየር ማረፍያ ቅርንጫፍ'' የሚሉት ነበሩ።

አቶ ሰለሞን በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰራሁባቸው አመታት በሥራ አጋጣሚ በደንብ ያወኩበት ጊዜ ነበር።አቶ ሰለሞን አሁን ድረስ በሕይወቴ የማልረሳው ሰው ነው።ትልቅ ትንሽ የለም ሁሉን ያከብራል።ትህትናው ነገሮችን የሚያስረዳበት አግባብ ሁሉ ምናልባት ከሺህ ሰው አንድ ይገኝ ይሆናል።በኃላ በሥራ አጋጣሚ እንደተረዳሁት ከልጅነቱ ጀምሮ ኮትኩታ ያሳደገችው የመንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል (ግቢ ገብርኤል) ሰንበት ትምህርት ቤት ''አምደ ሃይማኖት'' ለእርሱነቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገች ለማወቅ ችያለሁ።ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን አቶ ሰለሞን እኔ እዚያው መስርያ ቤት እያለሁ ወደ አሜሪካ መሄዱ ነበር።በአቶ ሰለሞን መሄድ በመላው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሰራተኞች በጣም ማዘናቸው ትዝ ይለኛል።

የሐዋሳው ባንክ ሥራ አስኪያጅ የገጠማቸው ፈተና 


በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አየር ማረፍያ ቅርንጫፍ ስራዬን በጣም ወደድኩት።በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወቅቱ ከነበሩት ቅርንጫፎች ውስጥ ለሰራተኞቹ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ለአየር ማረፊያ ቅርንጫፍ እና ለአቃቂ ቅርንጫፍ ነበር።ይህ የሆነበት ምክንያትም አየር መንገዱ ውስጥ ለመግባትም ሆነ ወደ አቃቂ ቅርንጫፍ ለመሄድ በቀላሉ ታክሲ ስለማይገኝ የሰራተኛ ማኅበሩ በህብረት ስምምነቱ ላይ ከተደራደረበት የመብት ጥያቄ ውስጥ አንዱ የሁለቱ ቅርንጫፎች ጉዳይ ነበር።በመሆኑም ከወሎ ሰፈር አየር መንገዱ ውስጥ የሚሄድ ሰርቪስ ማግኘቱ ለእኔ ተስማምቶኝ ነበር። በሌላ በኩል ንግድ ባንክ አሰራሩም ሆነ ያለው ዓለም አቀፍ አሰራሩ ሁሉ እንደ ሌላ መስርያቤት በቀላሉ ለሥርዓት አልባ ሰራተኛ አመቺ አይደለም። በእርግጥ በዘመነ ኢህአዴግ በተለይ ገና ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ሰሞን የባንክ አሰራርን ባህሪ የማይረዱ ካድሬዎች እንደ ግላቸው ሊያዙት ሞክረው ነበር።

እዚህ ላይ አንድ አስቂኝ ታሪክ በወቅቱ የነበሩት የቅርንጫፋችን ሥራ አስኪያጅ የነገሩኝ አሁን ድረስ ያስቀኛል።ሥራ አስኪያጁ በወቅቱ ሐዋሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንታት ነበሩ።ታሪኩ እንዲህ ነው።

ወቅቱ   ኢህአዴግ ገና ስልጣን መያዙ ነበር።አንድ ቀን ጧት ሥራ ላይ እያለን ሁለት ታጣቂዎች የታጀበ አንድ የደቡብ ክልል ባለስልጣን ወደ ሥራ አስኪያጁ ይጠጋና ማነጋገር ይጀምራል።በጉዳዩ ላይ ባለመስማማት እራሳቸውን ስነቀንቁ ከማዶ ሆኘ እመለከታለሁ።በኃላ እንደተረዳሁት ሥራ አስኪያጁ ነገሩ ግራ ቢገባቸው  ከባንኩ ሌሎች ኃላፊዎች ጋር ልነጋገር ይሉ እና ሰዎቹን አሰናብተው የዛሬውን የቅርንጫፋችን ሥራ አስኪያጅ የያኔውን የሐዋሳ ባንክ ቅርንጫፍ አካውንታት እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ይሰበስቡ እና ጧት ስለመጡት  ሰዎች ይነግሯቸዋል።ጉዳዩን በኃላ እንደተረዱት ከኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ባንኩ ውስጥ ኃላፊ ሰው መመደቡን እና  ደብዳቤ መያዛቸውን እንግዶቹ ለስራ አስኪያጁ ገልጠው ኖሯል።ሥራ አስኪያጁ የባንክ ሥራ በምድብ ሳይሆን በባንኩ ቅጥር በኩል ማለፍ እንዳለበት እና ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ማመልከት እንዳለባቸው ነግረዋቸዋል።ሆኖም ሰዎቹ አልተስማሙም።የክልሉን ጉዳይ የሚመለከተው ክልሉ እንጂ አዲስ አበባ አለመሆኑን በዘመኑ የብሄር ብሔረሰቦች መብት ንግግር ይናገራሉ።ይልቁንም  በሥራ አስኪያጅነት የተቀመጠ ሰው እንዴት የአገሪቱን ለውጥ አለማወቁ በስራው ላይ የብቃት ችግር እንደሚያሳይ በቁጣ ይናገራሉ። አሁን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሥራ አስኪያጁ ለመመካከር ይህንን ስብሰባ ለመጥራት መገደዳቸውን ገለጡልን ።
''መጨረሻው ምን ሆነ?'' ብዬ ጠየቅሁ።የቀድሞው አካውንታት የአሁኑ ሥራ አስክያጃችን ሳቃቸው እንደመጣ ሁኔታውን ማብራራት ጀመሩ።'' ከሁሉ በወቅቱ የገረመን ዋናው መስሪያ ቤት ጉዳዩን መፍታት አልቻለም።ግን ብልህ ሰዎች ነበሩ።ነገሩን ከክልሉ ጋር መፍታት ሳይችሉ አንድ ዘዴ አመጡ።ይሄውም ለግለሰቡ  ለጊዜው የስራ አስኪያጅ ወንበር እና ትልቅ ጠረንጴዛ እንዲሰጠው እና ትኬቶች እና ሰነዶች ላይ ግን እንዳይፈርም የሚል ነበር።በተጨማሪም ደሞዙን የደቡብ ክልል እንደሚከፍል እና ባንኩ ምንም ወጪ እንደማያወጣ ተነገረን። በመሆኑም ግለሰቡ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ያክል በትልቅ ወንበር ላይ ተቀምጠው ጋዜጣ እና መፅሄት ሲያነቡ አንዳንዴ የባንኩን ማንዋል ሲመለከቱ እና በባንኩ ሂሳብ ስልክ ሲደውል ከርሞ አንድ ቀን ክልሉ ሌላ ሹመት ስለሰጠው ቅርንጫፉን ለቆ በመሄዱ ትልቅ እፎይታ ተፈጠረ'' አሉኝ። 

''ራንዴቭኦ ሊንጋፎን ''የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት  እና ወጣት ትሑት ዘመድ 

ንግድ ባንክ ሥራ እንደጀመርኩ የምሽቱን ጊዜ በከንቱ እንዳያልፍ እፈልግ ስለነበር እና የፈረንሳይኛ ቋንቋ ለማወቅ ጉጉት ለነበረኝ በእዚያን ጊዜ ዋናው ፖስታ ቤት የሚገኘው ''ራንዴቭኦ ሊንጋፎን'' የቋንቋ ትምህርት ቤት ፈረንሳይኛ መማር ጀመርኩ።በእዚህ ትምህርት ቤት በቆየሁበት ጊዜ  ውስጥ ግን ቋንቋውን ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ የማልረሳቸው ጥሩ ሰዎችን ያወኩበት ነበር።ከእነዚህ ውስጥ አንዷ እና ዋናዋ ትሑት ዘመድ ትባላለች።ትሁት የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በናዝሬት ስኩል ተምራለች በወቅቱ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የላይብረሪ ሳይንስ እና ኢንፎርሜሽን ትምህርት ተምርቃ መጨረሷ ነበር። በተለይ ከትምህርቱ በኃላ በክፍል ውስጥ ከነበርነው ተማሪዎች ውስጥ ወደ ቦሌ መስመር የምንሄደው አብረን የምናወራበት ጊዜ እንዳያንስ ታክሲ ይዞ መሄድ ትተን እስከ መስቀል አደባባይ በእግር መምጣት አልያም ማኅተመ ጋንዲ መታሰብያ ሆስፒታል ፊት ለፊት ከሚገኙት የጭማቂ ቤቶች ገብቶ ማውራት በዓላት ባሉበት ቀናት ደግሞ  ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሄደን ተሳልሞ መሄድ ስራችን ነበር።

ትሑት ከሁላችንም የበሰለ አስተሳሰብ ያላት ነች።የአንድ ሰው ጥሩነት እና መጥፎነት ለማወቅ ደቂቃ አይፈጅባትም።ለጫወታ እና የሚያስቁ ነገሮችን አስፍታ እና አጉልታ በማቅረብ የሚያክላት የለም።ብሽሽቅ ከተጀመረ የዛሬ ወር የነበረ ታሪክ ጋር አገናኝታ ማብሸቅ ትችልበታለች።ትንሽ ቆይታ ደግሞ ትራራና ማሳሳቅ ትጀምራለች።

አንድ ቀን ''ስንነጋገር በፈረንሳይኛ ብቻ ይሁን'' አለችን።
እኛ ምኑን አውቀን? አልናት።'
'የምናውቃትን ቃላት እየገጣጠምን ማውራት ነው እንዲህ እየተባለ ነው የሚለመደው'' አለች።ትሑት ለካ የተወሰኑ ቃላትን የሸመደደችበት ቀን ነበር እና ግሱን ሳታዛንፍ ታወራን ጀመርን ተደነቅን።እኛ ገና ''ስምህ ማነው?'' ያለፈ ችሎታ ስላልነበረን።እንዴት ባንዴ አወቅሽ? ብለን ወጥረን ያዝናት።እርሷ ለካ ቀን አረፍተ ነገሮችን በእጇ ላይ ፅፋ ተዘጋጅታ ሲጠፋት  ዘወር እያለች ነበር የምትነግረን።ይህንንም የነገረችን በዕለቱ ነበር።አላስቻላትም። ትሑትን ታክሲ ሲያዝ አስቀድሞ ማስገባት የግድ ነው።አለዝያ ወደረዳቱ ጠጋ ብላ ሂሳቡን ሰጥታ ትገባ እና ሂሳብ ልትከፍሉ ስትሉ የታክሲው እረዳት ''ተከፍሏል''ሲላችሁ ወደ ትሑት መመልከት ነው።ያን ጊዜ ቆጣ ብላ ''እና ምን ልትል ነው?የተከፈለ እንደሆነስ?'' ብላ በቁጣ መልስ ታሳጣለች። ለእዚህ መፍትሄው ወደ ታክሲ ስትገባ ከረዳቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳታደርግ ማድረግ ብቻ ነው።

ትሑት ከሁሉ የሚገርም  ሌላም ባህሪ ነበራት።የተቸገረ ሰው ስታይ ሀዘኗ ምን ያህል ልቧን እንደሰበረው ከፊቷ ላይ ይታያል።''የእኔ ቢጤ'' ካጠገቧ መጥቶ ሲለምን ሳንቲም መስጠት ያሳቅቃታል።ጭብጥ አድርጋ አንድ ብር ትሰጣለች።ይህንን የሚያውቁ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን የነበሩ ''የእኔ ብጤዎች'' ሌላ ቀን እዝያው ለመሳለም ስንሄድ ከመቀመጫ ተነስቶ ያክል የቀረው ሰላምታ እና ምርቃት ያዥጎደጉዱልናል።አንድ ቀን እንዲሁ ትልቅ ፌስታል ከቦርሳዋ በተጨማሪ ይዛ ወደ ክፍል መጣች። ከክፍል እንደወጣን ''ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አለብን'' አለችኝ።
ቀኑን ሳስበው ምንም በዓል የለም።ዝናብ መጥቷል እና ''አሁን እንደርሳለን?'' ጥያቄ አቀረብኩ።'
'የግድ ነው።እስከ ፍላሚንጎ ታክሲ ይዘን መሄድ እንችላለን'' አለችኝ። 
አንዳንድ ቀን ለእግዚአብሔር ሳልነግረው ማደር የለብኝም የሚባል ጉዳይም አለ እና ''እሺ ! '' ብዬ አብረን ሄድን በቦሌ በኩል ባለው የቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ በኩል እንደገባን ''መጀመርያ ይህንን ዕቃ ለእማማ መስጠት አለብኝ''አለች እና ወደ ቤተ ክርስቲያኑ የአፍሪካ ህበረት በር በኩል ወዳሉት  ለልመና የተቀመጡት እናት አቅጣጫ አመራች። ትሑት ''እማማ'' የምትላቸውን እናት አውቃቸዋለሁ።በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ምዕራብ በር በኩል የሚቀመጡ እናት ናቸው።ትንሽ ነገር ስትሰጡዋቸው ምርቃታቸው ከልብ ነው። ትሑት ደግሞ ከልቧ ትሳሳላቸዋለች።ያን ቀን በፌስታል የያዘችውን ቀስ ብላ ''እማማ እንዴት አመሹ? ይችን ዕቃ አምጥቸልዎታለሁ'' አለቻቸው። እማማ የቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ሊዘጋ ገርበብ በማለቱ እና ዝናቡ መጣሁ እያለ በማጉረምረሙ ይመስላል ጭብጥ ብለው መሬቱ ላይ ተኝተው ላስቲክ ከላያቸው ላይ ደርበዋል። ስማቸውን ትሑት ስትጠራ ቀና አሉ። ያመጣችላቸውን ፌስታል ቀና ብለው ተቀብለው በእጃቸው ዳበሱት ልብስ እና ጫማ እንደሆነ ወድያው አወቁት  ከደስታቸው የተነሳ እንባቸው ዝርግፍ  አለ። 

ትሑት  ብዙ መቆየቱ ስሜታቸውን መጉዳት እንደሆነ ገብቷታል እናም ቶሎ ብላ ''በሉ ደህና እደሩ ቀሰቀስኩዎት? ይቅርታ! እማማ'' እያለች እኔ ወደ ቆምኩበት መምጣት ጀመረች። እማማ ግን መልሰው ጠሯት። ''ልጄ ቤትሽ የት ነው? በምሽት ይህን ተሸክመሽ፣ ተባረኪልኝ! ብቻሽን ልጄ!'' አሉ እና ቀና ብለው አዩኝ። ትሑት ''ይሄው ወንድሜ አለ'' አለቻቸው።''ወንድምሽ ነው? ተባረኩ በደከመ አቅማቸው ቀስ ብለው ተነሱና እጆቻችንን ይዘው ሳሟቸው። ''ተባርኩ እናት አባታችሁን ይባረኩ።እጆቻችንን ሲስሙ የእንባቸው ጠብታ እጆቼ ላይ አረፉ።ትሑት ቀድሞ የነበረው ለተቸገረ ማዘን ይብስ ተቀሰቀሰባት።እንባዋ ወድያው መውረድ ጀመረ።እማማን ተሰናብተን ተመልሰን ፍላሚንጎ ጋር ቆመን ታክሲ ስንይዝ ሁሉ በተሰበረ ልብ ነበር።ትሑት መኖርያ ቤቷ በጃፓን ኤምባሲ መግቢያ ገባ ብሎ በመሆኑ እኔ ቀድሜ ሰፈሬ ወሎ ሰፈር ላይ ወረድኩ።ታክሲው ከመቼው ሰፈሬ እንደደረሰ አላውቅም።ብቻ በሃሳብ ተውጠናል።በድንጋጤ፣በሃዘን እና በተሰበረ ልብ ሆነን እማማን እያሰብን ነበር የታክሲ ጉዟችን።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛዋ ትሑት ዘመድ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አየር ማረፍያ ቅርንጫፍ ሥራ የሚጀምረው ከጧቱ 2 ሰዓት ነው።ይህ ማለት ሰራተኛው ቢያንስ ቀድሞ 15 ደቂቃ ገብቶ ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት።ይህ ቅርንጫፍ ከሌላው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚለየው ባብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው ለፈጣኖቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች መሆኑ ሲሆን እነርሱ ደግሞ ከስራ ገበታቸው ተነስተው ወደ ባንኩ መጥተው የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት መስጠት ግዴታችን ነበር።ምክንያቱም ጊዜ የላቸውም።የስራ ሰዓት 'ዲሲፕልናቸውም' እጅግ የሚያስደስት በመሆኑም 2 ደቂቃ ማርፈድ ማለት ትልቅ ቀውስ የመፍጠር ያክል ነው።

አንድ ቀን ቀትር ላይ  ከስራ ሰዓት ቀድሜ ምሳ እንደጨረስኩ በሥራ ገበታዬ ላይ ሆኘ ጧት የተሰሩ ትኬቶችን አስተካክላለሁ።ባንኩ ገና የምሳ ሰዓት አገልግሎት መስጠት ያልጀመረበት ጊዜ ነበር እና በምሳ ሰዓት ደንበኛ ወደ ባንኩ አይመጣም።በመካከል እኔ ወዳለሁበት ወንበር  የጥበቃው ሰራተኛው መጥቶ  ጮክ ብሎ -
''ጌች  ሰው ውጭ ይፈልግሃል። ሰዓት ስላልደረሰ ጠብቂ ብላት ጥራልኝ አለችኝ'' አለኝ።  
በእዚህ ሰዓት ማነው? የፈለገኝ እያልኩ ከሃሳቤ ጋር እይተሟገትኩ ወደ ውጭ ወጣሁ። ከውጭ በኩል የባንኩን መከፈት የሚጠብቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ብዙዎቹ ከአየር መንገዱ ዩኒፎርም ጋር እንዳማረባቸው ቆመዋል።የማውቃቸውን ሰላምታ እየሰጠሁ እናባንኩ ሊከፈት የቀረው 10 ደቂቃዎች ነው የሚል የማፅናኛ ቃል እየተናገርኩ።ወደ ፈለገኝ ሰው ፍለጋ አይኖቼን ወረወርኩ። ትሑት ነበረች።በጣም መደሰቷ ከፊቷ ይታወቃል።የዕለቱን ደስታዋን  ለመንገር ቃላት አጥሯታል። ባጭሩ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት ማለፏን ልትነግረኝ ነበር። 

ትሑት ለበረራ አስተናጋጅነት ትክክለኛ ሰው እንደሆነች አውቃለሁ።ይህ ደግሞ እግዚአብሔር በሰጣት ውበት ብቻ አይደለም እንደስሟ ሰውን በጥንቃቄ እና በትሑትና የማናገር እና  የመርዳት ፍላጎቷ ብቻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትሑትን የመሰለች ሰራተኛ በማግኘቱ በጣም እድለኛ ነው አልኩ።እውነት ለመናገር የመስርያቤቱን የቅጥር ክፍልም አደነኩት።የሰው አመራረጡ በትክክለኛ መስፈርትም  በመምረጡ።

በቀጣዩ ጊዜያት ትሑት የአየር መንገዱ አስተናጋጅነት ስልጠና ስትወስድም ሆነ ከተመረቀች በኃላ በሥራ ላይ እያለች የወር ደሞዝ ለመውሰድ ወደ ባንኩ ስትመጣ በቀጥታ እንደምትቸኩል መንገር እና ቼኩን ከጀርባው ፈርማ ከመታወቂያ ጋር ቶሎ እንዳሳልፍ ሰጥታኝ ገንዘብ ቤት መጠበቅ ነው።ደንበኛን በፍጥነት እና በጥራት ማስተናገድ ደግሞ ስራዬ ነው።ያውም ለትሑት ሆኖ። ትሑት እኔ በሌለሁበት ቀን ከመጣች የስራ ባልደረቦቼ እንደ እኔ ሆነው ማስተናገዳቸውን እና ውለታ እንደዋሉ እየቀለዱ የሚነግሩኝ ብዙ ጊዜ ነበር። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 961 እና ህዳር 14 

ቀኑ ቅዳሜ ህዳር 14 ቀን ነው። የአዲስ አበባ አየር እንደ ወትሮው በውብ የፀሐይ ብርሃን እና ነፋሻማ አየር ሆድ ያባባል።ከረፋዱ 4:30 ገደማ ከባንኩ ውጭ ማክያቶ ጠጥቼ ተመልሼ ወደ ባንኩ እየገባሁ ነው።ከኃላዬ የበረራ አስተናጋጅ ወ/ሮ የሺመቤት ሁለት ልጆቿን ይዛ ባንድ እጇ የአየር መንገድ ቼክ ይዛ ጠራችኝ ዘወር አልኩ።

''ሳትገባ ይችን ቼክ ቶሎ ካሽ አስደርግልኝ መጣሁ አሁን በረራ አለኝ'' አለችኝ ብላ ከቼኩ ጀርባ ፈርማ ከመታወቂያዋ ጋር ሰጠችኝ። ወድያው የባንኩን ካውንተር ሳላልፍ ከውጭ ሆኘ ለተናኘ ለባንኩ ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ፊርማ አረጋጋጭ ሰጠሁ።ተናኘ ፈገግታ በማይለያት መስተንግዶ ''ኦ! የሺእመቤት'' አሁን አላየኃትም እንዴ?'' አለች እና ፊርማውን አረጋግጣ ቼኩን ወደ ገንዘብ ክፍል አሳለፈችው።ወዲያው የሺመቤት መጣች።ቼኩ ማለፉን ነገርያት ገንዘቧን ይዛ አመስግና ሕፃናት ልጆቿን ለሚረከባት ሰው ሰጥታ፣ አቅፋ እና ስማቸው  ወደ በረራዋ አመራች።ወደ በረራ ቁጥር 961።

ህዳር 14 ቀን 1989 ዓም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767፣ የበረራ ቁጥር 961  አስራሁለት የበረራ አስተናጋጅ፣ ካፒቴን ልዑል አባተ (የሺ እመቤት እና ወጣት ትሁት ዘመድም በረራው ውስጥ አሉ)  እና 163 መንገደኞችን ይዞ ወደ አቢጃን  አቀና።ከበረራው ጥቂት ደቂቃዎች በኃላ ግን አይሮፕላኑ ተጠለፈ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት ወር 1998 ዓም የበረራውን ጠለፋ አስመልክቶ ባቀረበው የውስጥ ሪፖርት ላይ እንደገለፀው አይሮፕላኑ ከምድር እንደለቀቀ ከ20 ደቂቃዎች በኃላ ሶስት ጠላፊዎች በፍጥነት አይሮፕላኑን እንደጠለፉት እና ማንም ተሳፋሪ እንዳይንቀሳቀስ እንዳስጠነቀቁ ሪፖርቱን ይጀምራል።ሁለቱ ጠላፊዎችም በፍጥነት ወደ ካፒቴን ልዑል የበረራ ክፍል ገብተው ብዛታቸው 11 እንደሆነ እና አይሮፕላኑን ይዞ ወደ አውስትራሊያ እንዲበር በኃይል እና በጉሸማ ነገሩት።ካፒቴን ልዑል አይሮፕላኑ ነዳጅ እንደሌለው እና አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ደጋግሞ ነገራቸው።ጠላፊዎቹ ግን በአየር መንገዱ ''ሰላምታ'' የተሰኘው መፅሄት ላይ  ቦይንግ 767 ለ11 ሰዓታት ነዳጅ ቆጥቦ እንደሚበር አንብበናል እያሉ አዋከቡት።ካፒቴን ልዑል በማስታወቂያ እና በነባራዊውሁኔታ መሃል ልዩነት መኖሩን እና በአሁኑ ወቅት ግን ነዳጅ እንደሌለው ደጋግሞ ነገራቸው።አልሰሙትም።

ካፒቴን ልዑል አባተ እጅግ አዘነ።ከእራሱ ሕይወት ይልቅ የተሳፋሪው ሕይወት አሳዘነው።አንድ አይነት ውሳኔ መወሰን እንዳለበት ተረድቷል።በሪፖርቱ ዝርዝር ላይ እንደተገለፀው የበረራ አስተናጋጅ ትሁት እና ፅጌረዳ በተቀመጡበት አንዱ አሸባሪ ሁለቱን ትክ ብሎ ከተመለከተ በኃላ ፅጌረዳ እንድትነሳ እንዳዘዛት ያትታል።በመካከል አሸባሪዎቹ ተሳፋሪዎቹን ለማስፈራራት ከካፕቴን ልዑል ክፍል ወጣ እንዳሉ ካፕቴን ልዑል የመናገርያውን ድምፅ ማጉልያ አንስቶ ተሳፋሪዎቹን በጠላፊዎች ላይ አንድ አይነት እርምጃ እንዲወስዱ አስታወቀ።በእዚህ ጊዜ ግን የአይርፕላኑ አንዱ ሞተር ስራውን አቁሞ አይሮፕላኑ ኮሞሮስ አጠገብ ወደ ሚገኘው ወደ ህንድ ውቅያኖስ እያሽቆለቆለ ነበር።በመጨረሻም አይሮፕላኑ በግራ ክንፉ በኩል ውቅያኖሱ ላይ ወደቀ።163 መንገደኞች፣ ያች ለሰው የምታዝነው ሩህሩህ እንደ ስሟ ትሑት የሆነቸው ወጣት ትሑት ዘመድ፣የልጆቿ ነገር የማይሆንላት  ሕፃናት ልጆቿንም ''መጣሁ! ቶሎ ነው የምመጣው'' ብላ የባንክ ቼክ ቶሎ እንዲመነዘርላት የጠየቀችው ወ/ሮ የሺመቤት ወ/መስቀል፣እውቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካፒቴን ልዑል አባተ ሁሉም ባህሩ ውስጥ ገቡ።የዓለም የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ''ሰበር ዜና'' ብለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 961 በኮሞሮስ ደሴቶች አጠገብ መከስከሱን ዘገቡ።
ኢትዮጵያ አየር መንገድ  ንብረት የሆነው ቦይንግ 767 ኮምሮስ ደሴት አጠገብ አደጋው ሲደርስበት 

በአደጋው ከበረራ ክፍሉ ባልደረቦች 
በሕይወት የተረፉ 
1/ ካፒቴን ልዑል አባተ፣
2/ ኦፊሰር ዮናስ መኩርያ፣
3/ የበረራ አስተናጋጅ ወ/ሮ የሺመቤት ገ/መስቀል፣
4/ የበረራ አስተናጋጅ ህይወት ታደሰ፣
5/ የበረራ አስተናጋጅ ግርማይ ለምለም እና 
6/ መካኒክ ሺበሺ መልካ ሲሆኑ 

ሕይወታቸው ያለፈው 
 1/ የበረራ አስተናጋጅ ፅገረዳ እስጢፋኖስ፣ 
2/ የበረራ አስተናጋጅ ዮዲት ሰብስቤ፣
3/ የበረራ አስተናጋጅ ትሑት ዘመድ አገኘሁ፣
4/ የበረራ አስተናጋጅ ፀሐይ ዘውዴ እና 
5/ የበረራ አስተናጋጅ ስሜ ጉልማ ነበሩ።

ከመንገደኞች ውስጥ 44ቱ ከአደጋው ሲተርፉ የቀሩት 119ኙ ሕይወታቸው አልፏል።

ዜናው በባንካችን ውስጥ እንደተሰማ ሁላችንም አለቀስን።እጅግ የሚያሳዝን በሕይወት የማይረሳ ስብራት ነበር።ሽብር እና አሸባሪን በዜና መስማት ይቀላል።እንደ ትሑት አይነት ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ማወቅ ግን የልብ ስብራት ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል።ሌላው አሳዛኝ ቀን የትሑት እና በአደጋው የሞቱ ኢትዮጵያውያን አስከሬን ቦሌ አየር መንገድ የደረሰ ቀን ነበር።

የትሑት አባት እጃቸውን እንዳጣመሩ በሃዘን የቆሰለ ሆዳቸውን ይዘው ወደ አየር መንገዱ አውቶብስ ገቡ።አስከሬኖቹ ከአውቶብሶቹ ፊት ሄዱ።ብዙ ሕዝብ ከውጭ ሆኖ ሀዘኑን በለቅሶ ይገልጣል።

ወጣት ትት ዘመድ 

ነገ ህዳር 14/2008 ዓም የትሑት እና የሌሎችን ሕይወት የቀጠፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 961 የሚረሳው የለም።አመታት ቢያልፉትም ዛሬ ድረስ እየቆየ ያሳቅቃል።ትሑት እና በአደጋው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቀብር የተፈፀመው ብዙ ሺህ ሕዝብ በተገኘበት፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስትተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ፣የእስልምና እና የሌላ እምነት ተከታዮች በተገኙበት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር ።በቀብሩ ሰዓት ከሚተራመሰው ሕዝብ መካከል ሆኘ ሳስበው ትሑት እንዲህ በአጭር ጊዜ ሕይወቷ መቀጠፉን መቀበል አልቻልኩም። አሁንም ድረስ እውነት አይመስለኝም።ሽብር ምን ማለት እንደሆነ ለማያውቁ ሽብር ማለት ይህ ነው።ፍፁም ንፁሃን እና የዋሃንን ካለ ጊዚያቸው መቅጠፍ።

ከቀናት በኃላ የበረራ አስተናጋጅ ወ/ሮ የሺመቤት ወደ ባንካችን ስትመጣ ሁላችንም እየወጣን አቀፍናት።ልጆቿን በግራ እና በቀኝ ይዛለች ስታየን እንባዋን ለቀቀችው።አልቅሳ አስለቀሰችን።ጥቁር በጥቁር ለብሳለች።ውስጧ ተጎድቷል።ወደ በረራው እየተጣደፈች ቼክ የሰጠችኝ ቀን የነበረችውን የሺመቤት ያየ ያን ቀን አያውቃትም።የደረሰባት ብርቱ ሃዘን ነበር።እርሷ በእግዚአብሔር ቸርነት ተረፈች።የሞቱት ሁኔታ ግን ልብ ይሰብራል።የሺመቤት ባንካችን በመጣች ቀን ከመሄዷ በፊት ትሑት ባህሩ ውስጥ ስትገባ ምን አለች? እንዴት እንዴት ነበር የሆነችው? ብዬ መጠየቅ አማረኝ።ጊዜውም፣ አግባብም አደለም።የሺመቤትን ሸኝተን ወደ ወንበሬ ተመለስኩ።የስራ ሰዓት መውጫዬ ሲደርስ እቤቴ ሄጄ ተኛሁ።ምሳም እራትም አላስፈለገኝም።ውስጥ ሲያዝን ምግብ ትዝ አይልም።ትሑት የበረራ አስተናገጅነቱን ሥራ ከጀመረች በኃላ ብዙም አልወደደችውም ነበር።ትምህርቷን መቀጠል እንዳለባት አምና ነበር። በበረራ በምትሳተፍባቸው ጊዜዎች ሁሉ ደግሞ ከበረራ በፊት ተንበርክካ ፀሎት ማድረግ ልማዷ ነበር።በሥራ ባልደረቦቿ ዘንድም''ያች ፀሎት የምታደርገው ልጅ'' በሚል ነበር የምትታወቀው።

በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ እና በተለይ ለትሑት ቤተሰቦች መፅናናቱን እመኛለሁ።እኛ ወደእነርሱ  እንሄዳለን እንጂ ያረፉት ወደ እኛ አይመጡም።በረራ 961 መሪር ትዝታ ይዞ አለፈ።እሱ አለፈ።ዛሬም ድረስ ጥቁር ትዝታው ግን አይጠፋም።



ጉዳያችን GUDAYACHN

ህዳር 13/2008 ዓም (November 23/2015)

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...