ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, June 22, 2015

አምስት መቶ አርባ ሰባቱ በደም የጨቀዩ ወንበሮች (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)




የኢትዮጵያ ጉዳይ ይሄው  መፍትሄ ሳያገኝ ዓመታት ነጎዱ።ባለጠብ መንዣዎች መሳርያቸውን በሕዝብ አናት ላይ ደግነው ''በሕዝብ ፍቃድ እና ምርጫ ነው ስልጣን ላይ ያለነው'' እያሉ ህዝብን ከመሳደብ በላይ ምን አይነት ሃገራዊ ውርደት ይገኛል? ኢህአዴግ/ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሃገራዊ ክብር፣የሕዝብ ልዕልና፣የትውልድ ሞራላዊ ስሜት ሁሉ ከሚታሰበው በላይ እንዲጎዳ ተደረገ።ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት በስም ጠንቅቀው ወደማያውቁት የአረብ ሃገራት ሁሉ ፈለሱ።በስርዓቱ የሚደገፉ እና የሚታገዙ የድለላ ቢሮዎች እስከ ታች ገጠር ድረስ መረባቸውን ዘርግተው እህቶቻችንን ለአረብ ባርነት ተሸጡ።በሀገራቱ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው የግፍ አይነት ለቁጥር ያዳግታል።የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስደት በአረብ ሃገራት ብቻ አይደለም በአፍሪካ ሃገራት በኬንያ፣ዑጋንዳ፣ታንዛንያ፣ሩዋንዳ፣ደቡብ ሱዳን፣ደቡብ አፍሪካ እና ሱማልያ ሳይቀር ትውልዱ ተበተነ።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ኢህአዴግ/ወያኔ ኢትዮጵያ እያደገች ነው እያለ በሀገር ውስጥ በአፈና ውስጥ በሚገኙት ሚድያዎቹ ይለፍፍ ነበር።በሀገር ውስጥም ዜጎች በሚናገሩት ቋንቋ እየተለዩ ከተወለዱበት ቀዬ እየተባረሩ በገዛ ሀገራቸውን  ስደተኞች ሆኑ። 

ከሐረር፣ጉርዳፈርዳ፣አምቦ፣ወልቃይት፣ጋምቤላ እና ሌሎችም ቦታዎች ዜጎች ካለምንም ጥፋት ተባረሩ።ቤተሰብ ተበተነ ልጆች የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆኑ።የኢህአዴግ/ወያኔ መንግስት በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለስደት፣ለውርደት፣ለሞት፣ለእስር እና ለስቃይ የዳረገ መንግስት ነው።በቅርቡ በሀገሪቱ ውስጥ በሕግ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተመዝግበው መወዳደራቸው ብቻ ከወንጀል ተቆጥሮባቸው የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ደም ሳይደርቅ ትናንት ሰኔ 15/2007 ዓም የኢህአዴግ/ወያኔ ምርጫ ቦርድ 547 መቀመጫ የያዘውን ምክር ቤት 100% የምክር ማሸነፉን አውጇል።

አምስት መቶ አርባ ሰባቱ በደም የጨቀዩ ወንበሮች 

ኢህአዴግ/ወያኔ የዛሬው 100% አሸነፍኩ የሚል የቅጥፈት ንግግር ላይ ለመድረስ ያበቃው እና ለጊዜው የቆመ ያስመሰለው ያፈሰሰው የደም ብዛት ነው።በያዝነው ወር ብቻ ብንመለከት የአረናውን ታደሰ አብርሃ ተሰቅለው ተገደሉ፣የሰማያዊ ፓርቲ ጠበቃ ሳሙኤል በስለት እና በዱላ ተገደለ።
በስለት እና በዱላ ጭንቅላቱ ላይ በሁለት ግለሰቦች የተገደለው የሰማያዊ ፓርቲ የ2007 ዕጩ 
ጠበቃ ሳሙኤል 

በደቡብ ክልልም የመድረኩ አባል እንዲሁ ሕይወታቸው ተቀጠፈ። እነኝህ ለናሙና ቀረቡ እንጂ ሌሎች አያሌዎች ከገጠር እስከ ከተማ ተገድለዋል።ከእዚህ ሁሉ በኃላ ባፈሰሰው ደም ጨቅይቶ እና ተረማምዶ ነው እንግዲህ ስርዓቱ አምስት መቶ አርባ ሰባቱ ወንበሮች በኢህአዴግ/ወያኔ መሞላቱ ዛሬ የተነገረን።ወዮ! በደም ለጨቀዩ አምስት መቶ አርባ ሰባቱ ወንበሮች።ቤቱ በራሱ በሺህ የሚቆጠሩ በእስር ቤት የሚማቅቁ ዜጎች እሪታም ጭምር የተሞላ ነውና። የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ቤተሰቦቻቸው መታሰራቸውን የማያውቁ አያሌዎች በማዕከላዊ መታሰራቸው ይነገራል።

የህክምና ዶክተሮች፣ፓይለቶች፣ኤሌክትሪሻኖች፣ጋዜጠኞች፣ተማሪዎች ወዘተ ቤተሰብ የት እንዳሉ ሳያውቅ በእስር የሚገኙ እና በእዚህም ዘመናት ያስቆጠሩ ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠራቸው።አንድ ቀን የእዚህ ሁሉ ግፍ አድራጊዎች ለፍርድ ሲቀርቡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታው ይገለጣል።በእስረኞች ሰቆቃ፣በግፍ በተገደሉት ንፁሃን ደም፣በስደት በሚማቅቁት ወገኖቻችን እና በህሊና እስረኞች ስቃይ ላይ ተረማምዶ አምስት መቶ አርባ ሰባት ወንበሮች የደረደረው የኢህአዴግ/ወያኔ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሕዝብ በምንም መስፈርት የህዝብ ተወካይ ወንበሮች ሊባሉ አይችሉም።በደም የጨቀዩ ወንበሮች ስብስብ ግን ሊባል ይችላል።በሐሰት ተጠንስሶ በሕዝብ ደም ለጨቀየ ወንበር ለመቀመጥ መስከረምን የሚናፍቁ ምንኛ ህሊናቸውን የሸጡ ናቸው? እንዴት  የሳሙኤል ደም፣የታደሰ አብርሃ ስቅላት፣የአብርሃ ደስታ፣የእስክንድር፣የርእዮት እና ሌሎችም ስቃይ፣የአንዳርጋቸው ፅጌ ሰቆቃ፣በአረብ ሀገር ከሰው ልጅ ክብር በታች የተዋረዱት እህቶች ዋይታ፣በሀገር ቤት የጥቂቶችን ቅምጥል ሕይወት እየተመለከተ በችግር የሚገረፈው ኢትዮጵያዊ መከራ አልታያቸው አለ? ለምን በደም ለጨቀየ ወንበር ተንገበገቡ? የሕዝብ ማዕበል ለሚፈነግለው የደም ወንበር ለምን ተንሰፈሰፉለት? የስርዓቱ አሽቃባጮችስ በንፁሃን ደም ባደፈ እጃቸው፣በሐሰት በረከሰ አንደበታቸው እና ይሉኝታ ባልቃኘው ህሊናቸው 547 በደም የጨቀዩ ወንበሮች በሐሰት አሸነፍን ለማለት እንዴት ተደፋፈሩ? 


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሰኔ 16/2007 ዓም (ጁን 23/2015)

No comments: