ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, May 26, 2015

እውን የኢትዮጵያን ችግር እንዳላዩ በማለፍ እና በቸልተኝነት የህሊና እረፍት ይገኛል? የእንቅልፍ ዘመናችን ያብቃ! ስለ ኢትዮጵያ ሁላችንም ያገባናል እንበል። (የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)


ኢትዮጵያን ዛሬ  ለደረሰችበት ደረጃ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋፆ ማድረጉን መካድ አይገባም።በቀጥታ ወይንም በተዘዋዋሪ በዝምታ።ከዛሬ 24 ዓመት ወዲህ ብዙዎች ኢትዮጵያን ብለው በእየእሥር ቤቱ ማቀዋል፣ተገርፈዋል፣ተሰደዋል፣ልጆቻቸው ካለ አሳዳጊ ቀርተዋል፣ሀብት ንብረታቸውን ተነጥቀው የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል።ለእዚህ ሁሉ መከራ እና ስቃይ የተዳረጉት ኢትዮጵያውያን ስለ ምንም ብለው አይደለም።ስለ ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ነው።

ለምን ይህ ሆነ?

ጋዜጠኛ እስክንድር በተሻለ ኑሮ ከሚኖርበት ከአሜሪካ ድረስ መጥቶ ማደርያውን ቃሊቲ ለምን አደረገ?
በቀለ ገርባ ከዩንቨርስቲ መምህርነቱ እስር ቤትን ለምን ቤቱ አድርጎ ኖረ? 
ፕሮፌሰር መስፍን እለት ከእለት የስርዓቱን ግልምጫ እና ጡጫ ችለው በጠባብ አፓርታማቸው ለምን ተኮራመቱ?
ዶ/ር ብርሃኑ ከተደላደለ ህይወቱ ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ ለእስር ለምን ተዳረገ? ቀጥሎስ ለምን ተሰደደ? 
አቶ አንዳርጋቸው ከእንግሊዝ ኤርትራ በረሃ ለምን ገቡ? ቀጥሎስ ወያኔ እስር ቤት ስቃይ ለምን እንዲቀበሉ ሆኑ?
ወጣቶቹ ዞን ዘጠኞች ለምን ብዙ ተስፋ ከሚጠብቃቸው ሕይወት እርቀው እስር ቤት ተወረወሩ? 
አሰፋ ማሩ በጠራራ ፀሐይ ለምን ተገደሉ?
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ለምን ተንገላታ? ለምን እስር ቤት ተወረወረ?
የመቀሌ ዩንቨርስቲ መምህሩ አብርሃ ደስታ እየሳቀ መኖር አቃተው? ለምን እውነትን በመናገሩ ብቻ ለእስር ተዳረገ?
የ1997 ምርጫ ተከትሎ ከአንድ መቶ ዘጠና ሶስት በላይ ኢትዮጵያውያን ለምን በጠራራ ፀሐይ በአዲስ አበባ ከተማ የጥይት አረር ሆኑ?
ሚልዮኖች ከሀገራቸው ወጥተው ለምን ተሰደዱ?

ብዙ መጠየቅ ይቻላል።እነኝህን ጥይቄዎች ለመመለስ ግን አንድ እና መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው።ኢትዮጵያ ከላይ ያነሳናቸው እና ያላነሳናቸው ሌሎች ኢትዮጵያን ብለው ለወደቁት እና ወህኒ ለተጣሉት ብቻ ነች እንዴ? የኢትዮጵያን ችግር እንዳላዩ በማለፍ እና በቸልተኝነት የህሊና እረፍት ይገኛል? አንድ ሰው ከህሊናው ጋር ካልተስማማ እንዴት መኖር ይችላል? ሕሊናን በምን መሸንገል ይቻላል? ስንቶች ለሞቱላት እና በእስር ለሚማቅቁባት ሀገር ያለንን እና የአቅማችንን ልናደርግላት ካልቻልን ኢትዮጵያዊነታችን ምኑ ላይ ነው?

አንዳንዶች ሀገሬን በነፃነት እንዳያት ምን ላድርግ? እኔ ምንም ማድረግ አልችልም።ብለው በተስፋ ቢስነት ይቀመጣሉ።ይህ ግን ፈፅሞ ስህተት ነው።በእዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ቢያንስ አንድ ሰው ብዙ ነው።አንድ ሰው ሃሳብ ማፍለቅ እና ዓለምን የማነቃነቅ አቅም እንዳለው የተመሰከረበት ዘመን ላይ ደርሰናል።ዛሬ አንድ ሰው ሃሳቡን ለመግለፅ የግድ የቴሌቭዥን ጣቢያ መጠበቅ ወይንም ዓለም አቀፍ መገናኛ ማማከር የለበትም።ከፅሁፍ እስከ ፊልም ድረስ ማናቸውም መልክቶች በደቂቃ ውስጥ ለመላው ዓለም ማሰራጨት ይችላል።

ኢትዮጵያውያን ምሁራንስ የት ናቸው?


ኢትዮጵያውያን ምሁራን በመላው ዓለም ተበትነው ድምፃቸውን አጥፍተው ለእራሳቸው እና ለቤተሰባቸው ብቻ የሚኖሩበት ዘመን ማብቃት አለበት።ከታሪክ አቅም በሙያው ባልሰለጠኑ በስሜት በሚነዱ ዘመነኞች ታሪክ እንደፈለገው ሲቀረደድ ዝም ማለት ኢትዮጵያዊ ያስብለናል? ዝምታ ያዋጣናል? ችግሩን እና መፍትሄውን ሻይ ቡና ሲሉ ብቻ ከወዳጅ ዘመድ ጋር በማውጋት የኢትዮጵያን ሕዝብ መድረስ ይቻላል? በተለይ በውጭ ያሉት የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥረው እና መድረኮች እየፈጠሩ ወጣቱን ማስተማር፣ማሳወቅ እና የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢ እንዲሆን እንዲሁም ለነፃነቱ እንዲቆም ማስቻል የምሁሩ ሥራ አይደለም? የነገዋን ኢትዮጵያንስ ከወዲሁ ማሳየት እና ለነገው ሥራ መጀመር ብሎም ማነቃቃት የምሁሩ ግንባር ቀደም ሥራ አይደለም?

ሌሎች በሀገር ቤት መከራ እና ስቃይ ሲቀበሉ ባህር ማዶ ሆኖ ዝምታ የት ያደርሳል? አዎን! ብዙዎች ሀገር ቤት ሲገቡ የሚደርሰውን ፈተና እና እዝያ ያለ ንብረት ደህንነት ሊይዛቸው ይችላል።ነገር ግን የኢትዮጵያ የአሁን ችግር በንብረት ጉዳይ በማውራት በእዚህ ደረጃ የወረደ ነው? ሌሎች ኢትዮጵያን ብለው ተሰደው ፈተና የደረሰባቸው ከሌሎቻችን በላይ ኢትዮጵያዊ ሆነው ነው? አይደለም።ይልቁንም ይህ ወቅት  በእዚህ ፍርሃት ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ነገር አለሙን ትተው በባህር ማዶ ሆነው የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚድያ ብቻ እየተከታተሉ ያሉቱኑ በእጅጉ የእነርሱም ሀገሬን ብለው መነሳት እና መንቃትን የሚፈለግበት ጊዜ ነው።የብዙዎች ዝምታ ጥቂቶች በኢትዮጵያ ላይ እንዲፈነጩ ዕድል ሰጥቷል።እኔ ለሀገሬ ነፃነት ምን እያደረኩ ነው? ምንስ ማድረግ ይገባኛል? ከእራሳችን ጋር ተማክረን መልስ ልንሰጠው የሚገባን ጥያቄ።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 18/2007 ዓም (ሜይ 26/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።