ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, May 13, 2015

ችግሩን ሁሉ በአቶ ኃይለማርያም ላይ በማሳበብ በስልጣን መዝለቅ አይቻልም።የኢትዮጵያ የችግሮቿ ምንጭ እራሱ ኢህአዴግ/ወያኔ ነው (ጉዳያችን)

አቶ ኃይለማርያም 

አቶ ኃይለማርያም  ደሳለኝ በፓርቲያቸው ሰዎች አንድ ቀን በፈጀ ግምገማ ክፉኛ መነቀፋቸውን እና እንባ እየተናነቃቸው ምላሽ መስጠታቸው እንዲሁም አቦይ ስብሃትን በተለይ ''ይጮሃል እንደ አሞራ ይዞረኛል'' እስከማለት መድረሳቸውን ኢሳት ራድዮ እና ቴሌቭዥን ግንቦት 5/2007 ዓም ባሰራጨው ዘገባ ገልጧል።

ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖሊሲውን፣በሙስና የታሹ የባለስልጣናቱን ነውር ሥራ እና የምጣኔ ሀብት ውድቀቱን ምክንያት ሁሉ በአቶ ኃይለማርያም ላይ አሳቦ ሕዝብን ማታለል አይችልም።አቶ ኃይለማርያም የአቅም ችግር እንዳለባቸው ዛሬ ነው እንዴ የታወቀው? አቶ ኃይለማርያምን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመረጡት አቶ መለስስ አይደሉም እንዴ? የእዚህን ያህል የአቅም ችግር እንዳለባቸው እየታወቀ አቶ መለስ ለምን አቶ ኃይለማርያምን  ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት መረጡ? መልሱ አቶ መለስ እራሳቸው የመምረጥ የአቅም ችግር ተጠቂ ነበሩ ወይንም እራሳቸው ጎልተው እንዲታዩ ሲሉ ሆን ብለው ከአቅም በታች የሆነ ሰው መርጠዋል የሚል ካልሆነ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ኢህአዴግ/ወያኔ የአቶ ኃይለ ማርያምን ግምገማ በተለይ አሁን ለምን እንደ አዲስ ለመተረክ ፈለገ? መልሱ ቀላል ነው።ኢህአዲግ/ወያኔ  ከገጠር እሰከ ከተማ ባለው ኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ከመቸውም ጊዜ በላይ 'አይንህን ላፈር' መባሉ ነው። በተለይ በሊብያ የወገኖቻችን መሰዋት እና እርሱን ተከትሎ በስርዓቱ የተወሰደው የቸልተኝነት ሂደት ይብሱን አዲሱን ትውልድ ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ/ወያኔ ተስፋ እንዲቆርጥ አደረገው። ለእዚህም ነው ከአስር አመታት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ  በአዲስ አበባ ወጣቶች የተሰማው።ይህ የህዝብ ቁጣ ማየል ስጋት ላይ የጣለው ስርዓት ታድያ አንድ አይነት መውጫ ይፈልግ ገባ።ለመውጫው ብቸኛ መንገድ ያደረገው ''ለችግሮች ሁሉ ምክንያቱ ኢህአዴግ/ወያኔ ሳይሆን  አቶ ኃይለ ማርያም ነው'' የሚል ተረታ ተረት ይዞ ቀረበ።ምናልባት ከምርጫው በፊትም ኢህአዴግ ባደረገው ግምገማ አቶ ኃይለ ማርያም ከስልጣን ወረዱ የሚል ዜና በመልቀቅ የህዝብ ጆሮ በማቆም እና ቁጣውን ወደ ሌላ ትኩረት ለማዞር ይሞከር ይሆናል።ይህ ሁሉ ግን ከንቱ ሙከራ ከመሆን አያልፍም።

ኢህአዴግ/ወያኔስ እንደ ድርጅት አቶ ኃይለማርያምን ሊቀመንበሩ እንዲሆኑ ሲመርጥ ገና ድርጅቱ የአቅም ችግር ያጥለቀለቀው መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሚስጥር አይደለም። ኢትዮጵያን በዕውር ድንብር ሲመራ የኖረው ድርጅት ዛሬ የሀገሪቱ ሀብት ተሟጦ ከሄደ በኃላ፣ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እንደቀረበው ሪፖርት ከ11 ቢልዮን ዶላር (ከ200 ቢልዮን ብር) በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ለማጣቷ፣ዜጎች በመላው ዓለም በተለይ በአረብ እና ጎረቤት ሃገራት እጅግ በተዋረደ መልክ ሕይወት መግፋት ለመጀመራቸው፣ኑሮ ውድነቱ ጣርያ ደርሶ ቤተሰብ የተባለ የሕብረተሰቡ አንዱ እና ዋናው አካል የፈረሰው፣ሙስና ቅጡን አጥቶ የሶስት ሺ ብር ደሞዝተኛ ባለስልጣን የአስር ሚልዮን ብር ቤት የሚሰራው፣ፍትህ መድረሻ አጥታ ዜጎች እንደ ከብት በእየእስር ቤቱ የሚታጎሩት እና ሌሎች ማለቅያ የሌላቸው የሀገሪቱ ችግሮች የተከሰቱት ድርጅቱ ኢህአዲግ/ወያኔ በአቅም ችግር የተወረረ በመሆኑ እና በሥርዓት አልበኛ ባለስልጣናት ስለሚዘወር መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል።አቶ ኃይለ ማርያም እራሳቸው የማን ውጤት ናቸው? አሁን በአስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ቆማችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ አታታልሉትም።ባጭሩ ስልጣኑን ለሕዝብ መልቀቅ ከመሰለ ብቸኛ አማራጭ ሌላ ለኢህአዲግ/ወያኔ ወርቅ የሆነ መንገድ ፈፅሞ አይገኝም።

በሌላ በኩል ግን አቶ ኃይለ ማርያምም ወደ ስልጣን እንደ መጡ አንስተውት የነበረው የሙስና ጉዳይ ተዳፍኖ ለምን ቀረ? ብሎ የመጠየቅ መብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።የሙስና ኮሚሽን ደብዛው እንዲጠፋ የተደረገው በህወሓት ባለስልጣናት አይደለም እንዴ? አቶ ኃይለ ማርያም ይህንን ሁሉ ጉዳይ የሚነግሩን ወቅት ይኖር ይሆናል አልያም እራሳቸው  ጣፋጭ ቀምሼ ነው ብለው ግለ ሂስ አድርግ ተብለው ይገደዱ ይሆናል።አቶ ኃይለ ማርያም በቀረቻቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ ማድረግ የሚችሉት በሙስና የተዘፈቁ ባለስልጣናትን በሙሉ ለፍርድ ማቅረብ አንዱ መሆን ይችላል።ከቤተ መንግስት አትክልተኛ ጀምሮ በአንድ ጎሳ እና በሙስና የተዘፈቀ ስርዓት ውስጥ ይህንን ማድረግ እንደማይችሉ የታወቀ ነው።አቶ ኃይለ ማርያም  የጦር ኃይሎች አዛዥ የሚል ማዕረግም ባለቤትም ናቸው ለካ!።እና ጦሩን ይዘዙት እንዴ? ማን ሰምቷቸው? 

 አንድ ሰሞን አቶ ኃይለ ማርያም ''ሙስና አጠፋለሁ'' ብለው ጮክ ብለው በሚናገሩባቸው እነኛ ወርቃማ ወራት ውስጥ (የዛሬ ሁለት ዓመት) ዋናው ኦዲተር በሀገሪቱ ያለውን የመንግስት ባለስልጣናት የአንድ ዓመት ብቻ  የሙስና ንቅዘት እንዲህ አስቀምጦት ነበር።

'- 1.4 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ ሒሳብ አለ፡፡
- 313.6 ሚሊዮን ብር ዕዳ ሳይመልሱ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡
- 897.5 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ክፍያና ወጪ ተደርጓል፡፡
- ያልተወራረደው 1.4 ቢሊዮን ብር በ57 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የታየ ነው፡፡
- 15 ድርጅቶች ወይም መሥሪያ ቤቶች ከልዩ ልዩ ገቢ ማስገኛ ምንጮች ገቢ የሚሰበስቡ ቢሆኑም፣ የገቢ   ሪፖርት የማያደርጉ በመሆኑ ኦዲት ማድረግ አለተቻለም፡፡
- በ13 ናሙና መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 132.364 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቧል፡፡
- 22 መሥሪያ ቤቶች 13.8 ሚሊዮን ብር ማስረጃ የሌለው ወጪ አድርገዋል፡፡
- 30 መሥሪያ ቤቶች ደንብና መመርያ በመጣስ 353.568 ብር የሚያወጣ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
- በውሎ አበልና በትርፍ ሰዓት ተመን 11 መሥሪያ ቤቶች 1.4 ሚሊዮን ብር አባክነዋል፡፡
- በኤርፖርት ተርሚናል የተሰማራ አንድ የግል ድርጅት ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ለመቀበል ፈቃድ ሳይኖረው ከአሥር ዓመታት በላይ እየሠራ እንደሚገኝና ተቆጣጣሪ አካላት ያደረጉት ምንም ነገር የለም፡፡
- 134.7 ሚሊዮን ብር ብድር ያልመለሱ የመንግሥት ድርጅቶች ሲኖሩ፣ የመንግሥት ትርፍ ድርሻ የሆነ 18.549 ሚሊዮን ብር ሳይከፍሉ የተሸጡ ድርጅቶች አሉ፡፡ 44.254 ሚሊዮን ብድር ያለባቸው ሲሸጡም የገዛው አካል ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ያልከፈለ መሆኑን ያስረዳ ነበር።

ይህ ሁሉ ተረሳና ዛሬ ሙሰኞቹ እራሳቸው አንድ አቅመ ቢስ ላይ ከበው አናት አናቱን ይሉ ገቡ።ባጭሩ የአቅም ማነስ ችግሩ የአቶ ኃይለ ማርያም ብቻ ሳይሆን የእራሱ ጎሳው ድርጅትም ጭምር ነው።ኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያን የምታክል ታላቅ ሀገር የመምራት አቅም የለውም።ችግሩን ሁሉ በአቶ ኃይለማርያም ላይ በማሳበብ በስልጣን መዝለቅ አይቻልም።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ግንቦት 6/2007 ዓም (ሜይ 14/2015)

No comments: