ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, November 17, 2014

የአንድ ወቅት የኮሜዲያን ልመነህ ቀልድ ለእዚህ ትውልድ ጥቂት ትምህርት ሳይኖራት አይቀርም። ፅሁፎቻችን፣የድረ-ገፅ ዘመቻዎችን እና ንግግሮቻችን ሕዝብ የሚያቀራርብ እንጂ የሚለያይ እንዳይሆኑ እንጠንቀቅ።(የጉዳያችን ማስታወሻ)

ኮሜድያን ልመነህ ታደሰ 

ልመነህ እና አጭር ኮሜዲው 
ኮመዲያን ልመነህ ታደሰ በአንድ ወቅት የኮሜዲ ሥራ ሲወሳ ቀዳሚ ስሙ የሚጠቀስ አርቲስት ነበር።ዛሬ ላለበት ሁኔታ አርቲስቶቻችን የሚያደርጉትን አንዳንድ ጥረቶች እያሞገስኩ (ድጋፎቹ በበቂ ደረጃ ናቸው ወይ? ለሚለው ጥያቄ መረጃ ባይኖረኝም) ይች በልጅነቴ የቀለዳት ቀልድን ማውሳት ፈለኩ።

 አጭር ኮሜዲ ድራማ - 
ሰውዬው ጎረቤቱን ሊከስ ፈለገ እና የሰፈሩን አንድ ወጣት ወደ ቤቱ ጠራው።ወጣቱን የፈለገበት ምክንያት የክስ ወረቀት እንዲፅፍለት ነበር።በመጀመርያ ያደረሰበትን በደል በቃል ነገረው፣ተረከለት በመጨረሻ ወጣቱ እንዲህ አለ ''ገባኝ እኔ ይህንን በደል በጥሩ ኪነ ጥበባዊ ፅሁፍ ከሽኘ ማመልከቻውን እስክፅፍልህ ግማሽ ሰዓት ስጠኝ'' ብሎ መፃፍ ጀመረ። ከግማሽ ሰዓት በኃላ ወጣቱ ለከሳሹ የፃፈውን ይዞ መጣ ለከሳሽም አነበበለት።

ወጣቱ ፅሁፉን ለከሳሹ ሲያነብለት ከሳሽ እንባው እየወረደ ነበር።በመጨረሻ ከሳሽ ማልቀሱን ማቆም አልቻለም።ወጣቱ ማመልከቻ ፀሐፊ ግራ ገባው።ቅድም ወደ ቤቱ ሲመጣ እንዲህ አልሆነም ነበር።አሁን የእርሱን ፅሁፍ ሲመለከት ይህን ያህል ማልቀሱ ግራ አጋባው።
ወጣቱ ጠየቀ - ''ምን ነካህ? ቅድም ጎረቤትህ ያደረሰብህን በደል ስትነግረኝ፣ያንን ሁሉ ታሪክ ስትተርክልኝ አላለቀስክም። አሁን የእኔን ፅሁፍ ስትሰማ ግን ማልቀስ ጀመርክ ጥላቻህም ባሰበት።ምንድነው ነገሩ?'' 

ከሳሽ መለሰ '' እኔ አሁን አንተ የፃፍከውን በደል ፈፅሞ አላውቀውም ነበር።እኔ በተራ ቃላት የማውቀውን በደል አንተ በከባድ ቃላት እና በስነ-ፅሁፍ ስታቀርበው የማላውቀውን በደል ስትነግረኝ ምንም እንኩአን አንተ ያልካቸው በደሎች ባይኖሩም ቢሆንስ ብዬ ጥላቻዬ ጨመረ።በጣም ነው የማመሰግንህ ያላደረገብኝን እና ያልተፈፀመብኝን ሁሉ ጨምረህ በስነ-ፅሁፍ አስውበህ በማቅረብህ።ቀድሞ በቀላሉ እናደድ የነበረውን ውብ በሆነ የፅሁፍ ችሎታህ የባሰ እንዳለቅስ ስላደረከኝ''

ወጣቱ ፀሐፊ ደነገጠ ማስታረቅ፣ሰላም ማውራት ሲገባው የባሰ ቤንዚን እየጨመረ መሆኑን ቆይቶ አወቀ።አንድነት ከመስበክ ይልቅ በደልን በኪነ-ጥበባዊ ፅሁፍ ከሽኖ ጎረበታሞቹን የባሰ ማጣላቱን አወቀ።የኮሜዲው መጨረሻ።

ወደ ዋናው ነጥብ ልምጣ  
በደል አለ።ማንም አይክደውም የበደሉን መጠን ለመለካት በደሉ የደረሰበትን ሰው ሆኖ መገኘት የግድ አይጠይቅም።ሰው መሆን በቂ ነው።ያለፈው የግማሽ ክ/ዘመን ታሪካችንን ብቻ ብንመለከት ደርግ በመላዋ ኢትዮጵያ ላይ ባደረሰው በደል ሁሉም የተነገረው ከተለያየ የስልጣን ፍላጎቶች አንፃር ነው።

በሰሜን ኤርትራ ለሚኖረው ሻብያ ''አንተ የተበደልከው ኤርትራዊ ስለሆንክ ነው'' አለው።
ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ '' አንተ ትግራይ በመወለድህ ነው'' አለው።
ወለጋ ላይ ኦነግ ''አንተ ኦሮሞ በመሆንህ ነው'' አለው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በደርግ ስርዓት ውስጥ የደህንነት ሚኒስትር ሆነው የሚሰሩት የትግራይ ተወላጅ ነበሩ።እራሳቸው ኮ/ል መንግስቱ የኦሮሞ ተወላጅ ነበሩ።የኮ/ል መንግስቱ የቅርብ አማካሪ የኤርትራ ተወላጅ ነበሩ።እንደ ዘር የተነሱት ጉዳዮች ከአምባገነናዊ ባህሪ እና ከስልጣን ሽምያው ጋር ሲነፃፀሩ የትዬለሌ ነበሩ።መሰረታዊ ችግሮቹ ግን የሕግ የበላይነት አለመከበር እና ሕዝባዊ መሰረት ያለው የእያንዳንዱን ግለሰብ ተሳትፎ ያላገኘ የመንግስት ስርዓት እንጂ የጎሳ ጥያቄዎች አይደሉም።ይህ ማለት የብሔር ጭቆና የለም።ፈፅሞም አልነበረም አሁንም የለም ለማለት አይዳዳኝም። ነገር ግን የችግሮች ሁሉ መፍትሄዎች ወደ ብሔር ፖለቲካ ማራገብ ከወሰድነው ወይንም በይሉኝታ እየተያዝን አንዱን ወገን እናስደስት በሚል ተነሳሽነት ብቻ ጎሳን ካራገብን የማንወጣበት አዘቅት ውስጥ እንዳንገባ ያስፈራል።

የጎሳ ፖለቲካ የችግራችን ሁሉ ምንጭም መፍትሄም አይደለም  
እዚህ ላይ አሁን ያለንበትን የስርዓቱን የጎሳ ፖለቲካ ችግር እና በአንድ ጎሳ የመጠቅለል አባዜ መቃወም እና አጠቃላይ 'የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የጎሳ ፖለቲካ ነው' ብሎ የመደምደም የመሃይም አስተሳሰብ መዳረሻው የት እንደሆነ አይታወቅም።የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ስልጣን መወጣጫ እስከመራቸው ድረስ የጎሳ ፖለቲካን ማራገብ እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት ይታያል።ይህ በአለማችን የተነሱ ጨካኝ አምባገነኖች የተከተሉት እኩይ መንገድ ነው።አሁን በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት እየተከተለው ያለው ይህንኑ መንገድ ነው።ስልጣን ከያዘ ከ23 ዓመት በኃላም ስሙን ''የትግራይ ነፃ አውጪ'' የሚል ነው። በእርሱ መንገድ በመሄድ ስኬት አይገኝም።የተቀናቃኝን ተቃራኒ በመያዝ ግን ስኬት አለ።ጎሳ ለሚያራግበው ህወሓት ሌላ ጎሳን ማራገብ መቃወም ሳይሆን መመሳሰልን ያስከትላል። የሀገራችን ገበሬ ምን ያህል ፊደል ቆጠርኩ ከሚለው መሻሉን እናስብፅሁፎቻችን፣የድረ-ገፅ ዘመቻዎችን እና ንግግሮቻችን ሕዝብ የሚያቀራርብ እንጂ የሚለያይ እንዳይሆን እንጠንቀቅ

ጉዳያችን
ህዳር 8/2007 ዓም (ኖቬምበር17/2014)

No comments: