ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 11, 2014

''አቡነ ዘበሰማያት ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም'' የዘጠኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለኃይማኖት ተቋማት ያስተላለፉት የፀሎት ተማፅኖን አስመልክቶ የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ


ኢትዮጵያ  በታሪክ ችግሮችን ከምትፈታባቸው  አንዱ እና ዋናው መንገድ  ፀሎት ነው።ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በተለይ ከፖለቲከኞች ስለ ሀገር እና ሕዝብ ፀሎት ይደረግ ብለው በግልፅ በጋዜጣው መግለጫ በታጀበ መልኩ የሃይማኖት አባቶችን ሲጠይቁ የሰማያዊ ፓርትን ጨምሮ ዘጠኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጀመርያዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም።ኢትዮጵያ መሪዎቿ ሀገራቸውን ከወራሪ ለመከላከል ሲነሱ ገዳማቷን ሳይማፀኑ እግራቸውን የማያነሱባት ሀገር ነበረች።የጥንቱን ትተን በቅርቡ ኢጣልያ ሀገራችንን በወረረ ጊዜ ንጉሡ አሁን ስድስት ኪሎ የሚገኘው ምስካህዙናን መድሃኔ ዓለም ታቦትን ወደ እየሩሳሌም ከዝያም ወደ እንግሊዝ  አብሯቸው መሰደዱ ይታወቃል። በተለይ ይሄው ታቦት  አምስት መነኮሳት አብረው ሌት እና ቀን ሳይለዩ የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲመለስ ሲማፀኑ እንደነበር እና በመጨረሻም ንጉሡ በስለታቸው መሰረት በድል የገቡበትን ሚያዝያ 27 ቀን ብቻ ታቦቱ እንዲነግስ ከእዚህ በስተቀር ግን ለጥምቀትም የማይወጣ ብቸኛ ታቦት መሆኑ ይታወቃል።ይህም ነፃነታችን የእግዚአብሔር ኃይል ውጤት ለመሆኑ ምስክር ነው።

ኢጣልያ በአድዋ ዘመቻ ድል ስትሆንም የኢትዮጵያ እና የእግዚአብሔር ግንኙነት በግልፅ የታየበት ነበር።ዛሬ አራዳ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ-ሕግ ከንጉሡ እና ከካህናቱ ጋር አብሮ ዘምቷል።እዚህ ላይ ታቦቱ እና ካህናቱ የዘመቱት ሰው ለመግደል ሳይሆን ሃይማኖት ለዋጭ፣ሀገር አፍራሽ የሆነውን  ወራሪ ኢጣልያን ሲዋጉ ለሚሞቱት የፍትሃት ፀሎት ለማከናወን እና ሰራዊቱን እና ንጉሱን ሃይማኖታዊ አገልግሎት ለመስጠት ነበር። ቤተ ክርስቲያን በደስታም በሀዘንም የመገኘቷን ያህል እልፍ አስከሬን እንደሚከመር በተረጋገጠበት የጦርነት ቦታ ተገኝታ ፀሎት ማድረግ  የቤተ ክርስቲያን ሥራ ካልሆነ የማን ሊሆን ይችላል?

እዚህ ላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ሚና ብትይዝም በስድስተኛው ክ/ዘመን የተነሳው እና ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ቀጥላ አማኞቹን ተቀብላ ያስጠለለችው የእስልምና ሃይማኖትም እንዲሁ በኢትዮጵያ የክፉም ሆነ የደስታ ጊዜ አልተለየም።ለእዚህም ማስረጃው አሁንም የአድዋ ጦርነት ወቅት ዘማቹ ከአዲስ አበባ አራዳ ቤተ ክርስቲያን ሲነሳ በነበረው የፀሎት መርሃ ግብር ላይ ሙስሊም ኢትዮጵያውያንም ፊታቸውን በተቃራኒው አድርገው የእራሳቸውን ፀሎት ማድረጋቸው እና ሳላት መስገዳቸውን የሚያሳዩ  በፎቶ ግራፍ የተደገፉ  ታሪካዊ ማስረጃዎች መገኘታቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው።

ባጠቃላይ ለፖለትካዊው ሆነ ለአጠቃላይ ሃገራዊ ችግራችን ፀሎት ማድረግ ዓለም ሳይጀምረው የጀመርን እና የተጠቀምንበት ሕዝብ ነን።ሆኖም ግን ፀሎትን እንደ ሞኝነት መቁጠር የጀመረ ትውልድ ከታቀፍን ደግሞ አርባ ዓመታትን ማስቆጠራችንን ልንረሳው አይገባም።አሁን በምንኖርበት ዓለም ከሕዝባቸው እስከ 80% የሚሆነው ምንም አይነት እመነት የሌለው ሕዝብ የሚመሩት የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ሳይቀሩ  እግዚአብሔርን መጥራት በየንግግራቸው መሃል የለመዱትን ያህል በፀሎት እዚህ የደረሰች ሀገር-የኢትዮጵያ መሪዎች ግን  አባት እና እናቶቻቸው የሚያውቁትን አምላክ እነርሱን ያልፈጠረ ይመስል በመገናኛ ብዙሃን መናገር የሚያፍሩ ናቸው።አንድ ወቅት የኢህአዲግን ምክርቤትን ሲከፍቱ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በንግግራቸው መጨረሻ ላይ ''እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ'' ሲሉ በመስማታችን ደስ ያለን ምስኪኖች መሆናችንን ልብ አላልነው ይሆን? ኢትዮጵያን የሚያህል ሀገር መሪዎቿ እግዚአብሔርን አይጠሩም እና ከአስርተ ዓመታት በኃላ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ''እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ''  የሚል ቃል ስንሰማ ብርቅ ሆነብን።ይህ በራሱ ከእኛነታችን ጋር በተቃረነ የደረሰብንን ስብራት ያሳያል።  

''እግዚአብሔር አሜሪካንን ይባርክ'' እያሉ የሚናገሩ መሪዎች በምንሰማማባት ዓለም ጥንታዊቷ በመፅሐፍ ቅዱስ ''እናንት እስራኤላውያን ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ አይደላችሁምን?'' የተባለልን ሀገር፣ አሁንም በመፅሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ብቻ ከአርባ ጊዜ በላይ ''ኢትዮጵያ'' የሚለው ስማችን የተጠራባት ሀገር፣ በእስልምናውም ዓለም በነቢዩ መሐመድ ''ኢትዮጵያውያንን አትንኩ'' ተብሎ የተነገረላት ሀገር መሪዎች እግዚአበሄርን አይጠሩባትም።ለእዚህ ነው ዛሬ  ለሀገራዊ ምስቅልቅል ችግሯ ከአርባ ዓመት በኃላ  የፖለቲካው ዓለም ተዋናዮች ለሀገራችን ችግር ፀሎት እናድርግ ብለው የሃይማኖት መሪዎችን ሲያሳስቡ ከመስማት የበለጠ ምን ደስታ አለ? የሚያስብለው።

የሃይማኖት መሪዎች ምላሽ 'ታላቅ' የሚሉት በስልጣን ላይ ያለውም አሳሰበ 'ታናሽ' የሚመስሉት ተቃዋሚዎችም አሳሰቡ ከእነርሱ የሚጠበቀው ''እግዚአብሔር አሳሰበን'' ብለው ፀሎት ማድረግ ነው።ፀሎት ፖለቲካዊ መልክ  የለውም። ፀሎቱን የሚሰማው አምላክም የምንም ፓርቲ አባል አይደለም።የእውነት እና የፍቅር ብቻ እንጂ። አዎን ዘመን ተቀይሯል።ትውልድም ተቀይሯል።ፀሎት እንደ አንዱ እና ዋናው  የችግር መፍቻ መንገድ ስትጠቀም የነበረች ሀገር ከፖለቲካ ተዋናዮቿ ፀሎት ለሀገራችን ይደረግ ብለው ለሃይማኖት አባቶች መልዕክት ሲያስተላልፉ መስማት እራሱ የትውልዱ እራሱን እና ማንነቱን የማወቁ ምልክት ነው።''አቡነ ዘበሰማያት ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም'' እንዲል ለሀገራችን መፍትሄ የተባለ ቅንጣት ታህል የመፍትሄ ሃሳብ ልታመልጠን አይገባም እናም ለጥቂት ደቂቃዎች አምላካችን ፊት የሀገራችንን አጀንዳ ማቅረብ አንርሳ!
በመጨረሻም የዘጠኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደረጉት የፀሎት ጥሪ ይህንን በመጫን ያንብቡ።

ጉዳያችን 
ህዳር 2/2007 ዓም (ኖቬምበር 11/2014)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።