ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, September 3, 2014

'ባለቤት አልባዋ' ከተማ የባለቤት ያለህ! እያለች ትጮሃለች በአዲስ አበባ በቅርስነት የተመዘገበው ህንፃ ቅርስ አይደለም ይፍረስ ተባለ

ሎምባርድያ ሬስቱራንት የሚገኝበት ህንፃ 

በየትኛውም ሀገር  ከተሞች ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ የሆኑ ህንፃዎች ማፍረስ በሕግ ያስቀጣል።አዲስ የሚሰራ መንገድም ቢሆን አቅጣጫውን ይቀይራል እንጂ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የሆኑ የከተማ ሕንፃዎችን አይነካቸውም።

እንደነ ናይጀርያ አይነቶቹም ሌጎስን አፍርሰው ሳይሆን ባለችበት ትተው አቡጃ በሚል አዲስ የንግድ ከተማ ሰሩ እንጂ የነበራቸውን የአጭር ዘመን ቅርስ ለማፍረስ አልደፈሩም።ለንደንም አሮጌዋ እና አዲሷ ለንደን በሚል እንጂ የነበረውን አፍርሰው የአዲሱን ትውልድ ሥራ አልተጫነባትም።የቀደሙት የሰሩት ለመጪው እንዲቆይ አስቀመጡት።

የባለ ቤት አልባዋ የአዲስ አበባ ጉዳይ ግን ከእዚህም ይከፋል። ብዙ ከመቶ ዓመታት በላይ የሚሆኑ ቅርስ እና ህንፃዎቿ በስመ-ልማት ፈርሰዋል።ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የተስፋ ገብረ ስላሴ ማተምያ ቤት ይፍረስ ተብሎ ልጆቻቸው እስከ አቶ መለስ ቢሮ ድረስ ደርሰው ''ከጎኑ የሚመጥን ህንፃ እንሰራለን የነበረው አይፍረስ'' ብለው አቤት ማለታቸውን ከጋዜጦች አንብበናል።

የዛሬው ጉዳይ ደግሞ የባለ ቤት አልባዋ ከተማ ቅርስ ተብሎ የተመዘገበውን ካድሬዎቹ መልሰው ቅርስ አደለም የሚል መግለጫ ሲሰጡበት የታየበት ነው።ነገሩ እንዲህ ነው።
ይህ  በፎቶው የምትመለከቱት ህንፃ መክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ዋቢ ሸበሌ ህንፃ አጠገብ ሉምባርዲያ ሬስቱራንት የሚገኝበት ነው።ህንፃው የተሰራው በ 1926 ዓም ነው።ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ነው።ስለህንፃው የቅርስ ምዝገባ ለማውሳት እነኝህን ነጥቦች እንመልከት -

  • - ታህሳስ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ህንፃውን የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት መመዝገቡን ለሚመለከታቸው ሁሉ አሳወቀ፣
  • - ይህንንም የወሰነው ከቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬትና ከቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት፣ እንዲሁም ከራሱ ቢሮ በተውጣጡ ባለሙያዎች በዝርዝር ተጠንቶ የቅርስ መሥፈርት እንደሚያሟላ አረጋግጦ መሆኑን ጭምር ገልፆ ነበር፣
  • - ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ታህሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ የሕንፃውን ቅርስነት አረጋግጦ ነበር፣
  • - በዚህ መሠረት የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤቱ እያዘጋጀ ባለው ማስተር ፕላን ላይ ሕንፃው ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት በባህል ቢሮው ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ሕንፃው ቅርስ መሆኑን አውቀው አስፈላጊው ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፡
  • - በያዝነው ወር ህንፃው ፈርሶ ሌላ ግንባታ ይደረግበታል ሲባል ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ ይፍረስ ያሉትን የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን ''በቅርስነት የተመዘገበ ህንፃ ለምን ይፈርሳል?'' የሚል ጥያቄ ጠይቆ ኃላፊው ለመመለስ ቃላት ሲያጥራቸው ተደምጧል።
  • ሽገር በያዝነው ወር ውስጥ ሲጠይቅ በቅርስነት የመዘገበው ክፍል ህንፃውን እንደመዘገበው ነበር።


 ዛሬ ነሐሴ 28/2006 ዓም በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣው ዘገባ ግን ''በባለሙያ አስጠንቶ ቅርስ ብሎ የመዘገበው አካል።''ቅርስ አይደለም ተዉት ሃሳቤን ቀይርያለሁ'' ብሏል።ባለቤት አልባ ከተማ ቅርስ ተብሎ የተመዘገበን ለአቅመ ''ከዛሬ ጀምሮ ቅርስ አደለምነት'' ደርሳለች።ነገ ሃውልቱም፣የእምነት ቦታዎችም ወዘተ ገንዘብ ይዞ የመጣ ሁሉ ቅርስ አይደሉም የማስባል  አቅም እንዳለው አሳየች።ሀገር ተሸጠች፣ባለቤት አልባዋ ከተማ የባለቤት ያለህ! እያለች ነው።

ጉዳያችን
ነሐሴ 28/2006 ዓም (ሴፕቴምበር 3/2014)


No comments: