ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, August 27, 2014

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እና የአማራ ዲሞክራሲ ኃይሎች ንቅናቄ የውህደት ስምምነትን በተመለከተ -የዜናው ይዘት፣ የውህደቱ ደረጃ ፣ውህደቱ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚጠናቀቅ እና የውህደቱ ዜና በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ኃይላት ዘንድ የሚኖረው ትርጉም (የጉዳያችን ጡመራ አጭር ጥንቅር)


ዜናው 

ነሐሴ 19/2006 ዓም ምሽት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) በሰበር ዜናነት የሚከተለውን ዜና አሰማ -
''በስልጣን ላይ ያለውን የኢህአዲግ መንግስት በተለያየ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች ወደ ውህደት የሚያደርሳቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር፣ የግንቦት7 የፍትህ፣የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ ናቸው።ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ትግላቸውን በአንድነት አቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል” ይላል። 
ድርጅቶቹ ያወጡት መግለጫ ይህንን በመጫን ይመልከቱ።
ከእዚህ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች የውህደቱን ደረጃ እና በምን ያህል ፍጥነት እንደሚከናወን የሚገልጡ ናቸው።

የውህደቱ ደረጃ 

ነሐሴ 20/2006 ዓም የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበበ ቦጋለ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሊቀመንበር አቶ መዓዛ ጌጡ የውህደቱን ደረጃ አስመልክተው ለኢሳት ራድዮ በሰጡት መግለጫ የውህደቱ ደረጃ -
1/ ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ ተዋህደው የቀድሞ ድርጅቶች ከስመው ሶስቱም አንድ ድርጅት እና በአንድ አመራር ስር እንደሚሆኑ፣
2/ አቶ አበበ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር ቃል በቃል እንዳስቀመጡት ''ዋናው ዓላማ ብሔራዊ የሆነ ነፃ አውጪ ኃይል መፍጠር'' መሆኑን መግለፃቸውን እና 
3/ የሶስቱም ድርጅቶች ሰራዊት በአንድ ዕዝ ስር እንደሚገቡ ገልፀዋል። 

ውህደቱ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚጠናቀቅ

የብዙዎች ጥያቄ የሆነው ውህደቱ በምን ያህል ፍጥነት የከናወናል? የሚለው ነው።ለእዚህ ጥያቄ የኢሳቱ ጋዜጠኛ አቶ መሳይ ለአቶ አበበ ቦጋለ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር ''ምናልባት የውህደቱን ጊዜ በጊዜ ማስቀመጥ ይቻላል?'' በሚል ላቀረበው ጥያቄ አቶ አበበ እንዲህ መልሰዋል -
''.....ይህ ውህደት በዓላማ እና በራዕይ ተመሳሳይ በሆኑ ድርጅቶች መካከል የተደረገ ነው.........አሁን ሂደታችንን በተመለከተ የውህደት ኮሚቴ ተመስርቷል ውህደቱን በወራት ምናልባት ቢዘገይ እሰከመጪው ጥቅምት 30 እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር ይጠነቀቃል ብለን እናስባለን.....ውህደታችን በጉልበት፣በገንዘብ እና በንብረት የተሻለ አቅም ይፈጥራል።በሂደትም ከሌሎች ድርጅቶች እንደ ትግራይ የነፃነት ድርጅት ጋር በጥምረትም ሆነ በትብብር የምንሰራበት ሁኔታ ይኖራል'' ብለዋል።

የውህደቱ ዜና በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ኃይላት ዘንድ የሚኖረው ትርጉም 

የውህደቱ ዜና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ መደመምን ፈጥሯል።በርካታ ተቃዋሚ ድርጅቶች በአንድነት መዋሃድ ሲሳናቸው ለዓመታት የሰማ ሕዝብ የሰሞኑ ዜና በትልቅ ብስራትነት ቢመለከት ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም።ይህ ጉዳይ ግን በውጭ ኃይላት ዘንድ የሚኖረው ትርጉም እንደሚለያይ መገመት ብዙም አስቸጋሪ አይደለም።በኢትዮጵያ ላይ ስልታዊ ጥቅም ያላቸው ኃይሎች ካላቸው ጥቅም አንፃር ለውህደቱ የሚሰጡት ትርጉም የተለያየ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
አንድ ነገር ግን ከወዲሁ ማለት ይቻላል።በተለይ የውጭ ኃይሎችን በተመለከተ።ይሄውም ሁሉም የውጭ ኃይሎች ባላቸው መረጃ የሚያረጋግጡት ጉዳይ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዲግ/ወይኔ የህዝብ ድጋፍ የራቀው ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱም በሙስና፣በርዕዮት ዓለም ቀውስ እና በስልጣን ሽምያ ችግር ውስጥ መሆኑን እና ወደውድቀት እያመራ ያለ መሆኑን ነው።
በሃያላኑ አንፃር ግን ጉዳዩ ከእዚህም እንደሚዘል ይታሰባል።የሄውም የለውጥ ተዋናይ የሆኑት ድርጅቶች  በኢትዮጵያ የሚያመጡት ለውጥ የሃያላኑን ጥቅም በአፍሪካ ደረጃም የሚጎዳ እንዳይሆን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ  ካንዣበበባቸው የፅንፈኛ እስልምና ኃይሎች ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት መስጠታቸው አይቀርም።
በመሆኑም ውህደት የፈጠሩት ኃይሎች በዓለም ዓቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተሰሚነትን የማግኘቱን ሂደት የውጭ ኃይሎችን ጥቅም  በማያስደነብር መልኩ ግን ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ዘለቄታዊ ጥቅም ባስከበረ አቀራረብ ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ የማማለል እና ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት ፖለቲካዊ ችግሮች በአማራጭ ኃይልነት ቶሎ እራሳቸውን ማቅረብ አለባቸው።ይህ እንግዲህ በሀገር በት ከሚኖረው ዋናው ትግል ጎን ለጎን የሚካሄድ ይሆናል ማለት ነው።

ጉዳያችን 
ነሐሴ 22/2006 ዓም (ኦገስት 28/2014)





No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።