ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 7, 2014

ሰበር ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች - ኢህአዲግ እና ተቃዋሚዎች ወሳኝ ነጥብ ላይ መሆናቸውን አውቀውት ይሆን? የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት ኃላፊ ዋሽግተን ገቡ፣የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩሳት ተቀስቀሰ፣ሩስያ ከመቸውም በበለጠ ደረጃ እየተፈራች ነው።(የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ማስታወሻ- ይህ ፅሑፍ ከሶስት ወር በፊት ሚያዝያ 16/2006 ዓም (April/2014) በእዚሁ ጡመራ ገፅ ላይ የወጣ እና ዛሬ እንደገና የተለቀቀ ነው።''የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ጊዜ የለም ''ይላል።
ካርታ ከ ቢቢሲ ሰኔ 2005 ዓም ከለቀቀው ዜና የተገኘ 

ሩስያ ከመቸውም በበለጠ ደረጃ እየተፈራች ነው

የዓለማችን ዓለም አቀፋውም ሆነ አካባቢያዊ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቀየሩ ነው።የዩክሬኑ ጉዳይ ከመሻሻል ይልቅ ከቀን ቀን እየተባባሰ መጥቷል።ሩስያ ከክሬምያ ህዝበ ውሳኔ በኃላ የምዕራባውያን ቁጣ ወደ ጎን በማለት ዩክሬን ያሉ አፍቃሪ-ሩስያውያንን ሁኔታ በአንክሮ እየተከታተለች ነው።ዛሬ ዩክሬን  በአፍቃሪ-ሩስያውያን ላይ በወሰደችው እርምጃ ከአምስት ያላነሱ መገደለቸው ሩስያን በእጅጉ ከማስቆጣቱም በላይ በዩክሬን ድንበር ላይ የጦር ልምምድ እያደረገች መሆኗ ተገልጧል።የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም በድጋሚ (ዛሬ) ለዩክሬን ማስጠንቀቅያ ሰጥተዋል።ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ ትናንት ቢቢሲ በድረ-ገፁ እንደገለፀው 'የእንግሊዝ አየር ኃይል የሩስያ አየር ኃይል የእንግሊዝን የአየር ክልል ለመጣስ ሲሞክር ተደረሰበት የሚል ዜና መልቀቁ ሲሆን ጉዳዩ ወደ መጎናተል ተሽጋገረ እንዴ? ለማለት ያስገድዳል።

የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት ኃላፊ ዋሽግተን ገቡ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከግብፅ አብዮት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ የተባለ የግብፅ ባለስልጣናት ወደ ዋሽግተን ለምክክር ተጉዘዋል።ባለስልጣናቱ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ናቢል ፋህሚ እና የደህንነት መስርያቤቱ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ሞሐመድ ኤል ቶሃሚ ሲሆኑ ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ጋር ዝግ ውይይት እንዳላቸው ''አህራም ኦን ላይን'' በድረ-ገፁ ገልጧል።አሜሪካ ባለፈው ሐምሌ ወር ለግብፅ ትሰጥ የነበረውን የወታደራዊ እርዳታ እንደገና እንደምትገመግም መግለጧ ይታወቃል።የሁለቱ ባለስልጣናት ጉብኝት ዋና አላማ አሜሪካን ለግብፅ ለመስጠት ተዘጋጅታ የነበሩና ያዘገየቻቸውን ታንኮች፣ሚሳኤሎች፣ተዋጊ አይሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች እና በተጨማሪም 260 ሚልዮን ዶላር የጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ እንድትለቅ ለማግባባት ጭምር እንደሚሆን ድረ-ገፁ ገልጧል።ከእዚህ በተለየ ድረ-ገፁ አይግለፀው እንጂ የግብፅ የወቅቱ ቁጥር አንድ አጀንዳ በኢትዮጵያ እየተሰራ ያለው የአባይ ግድብ ጉዳይ እንደሚነሳ መገመት ይቻላል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ትኩሳት ተቀስቀሰ

በሌላ በኩል ለዘመናት የአፍካ ቀንድ ሃገራትን እና ግብፅ ከአሜሪካን እና እስራኤል ጋር የሚኖራቸውን የግንኙነት መስመር የሚያዋልለው የመካከለኛው ምስራቅ ትኩሳት የመጨመር አዝማምያ እንደሚኖር የሚያመላክት አዲስ ክስተት መታየት ጀምሯል።ይሄውም የፍልስጤም ሁለቱ ባላንጣ ቡድኖች ማለትም በምዕራቡ በሚደገፈው የፍልስጤም ራስ ገዝ መንግስት እና በነውጥ የሚያምነው 'በሐማስ' መካከል ለእረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረው ውይይት ሰምሮ የመስማማታቸው ዜና ነው። አሜሪካ እና እስራኤል ከሐማስ ጋር የሚደረግ ማናቸውም ስምምነት እንደማይደግፉ በግልፅ አሳውቀዋል።እስራኤል በተለይ ከፍልስጤም ራስ ገዝ መንግስት ጋር የነበረውን ውይይት ለማቆም መገደዷን ገልፃለች። ይህ ማለት የመካከለኛው ምስራቅ የኃይል አሰላለፍ እንደገና አጃቢ ስልታዊ ሃገራትን ይዞ መቀስቀሱን ያመላክታል።የኃያላን ሃገራትም ትኩረት በአዲስ መልክ ከመሳቡ ባለፈ ትናንሽ የሚባሉ ሀገራትንም ስቦ ማስገባቱ አይቀርም።

ኢህአዲግ እና ተቃዋሚዎች ወሳኝ ነጥብ ላይ መሆናቸውን አውቀውት ይሆን?

ከላይ የተገለፁት የሩስያ የልዕለ ኃይልነት ስሜት መነቃቃት እና የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ መጋጋል የግብፅን ስልታዊነት አስፈላጊነት መጨመሩ እና ኢትዮጵያ ደግሞ ከግብፅ በበለጠ በአባይ ጉዳይም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ባላት የህዝብ ብዛት እና ወሳኝ ስልታዊ አቀማመጥ አስፈላጊነቷ መጨመሩ የማይቀር ብቻ ሳይሆን የምዕራባውያንን ትኩረት መሳቧ ሃቅ ነው። ይህ ማለት በኢትዮጵያ የሚነሳ ማናቸውም ተፅኖ ፈጣሪ የመደመጥ ኃይሉ ቀላል አይሆንም ማለት ነው። የአካባቢው ትኩሳት በመካከለኛው እና በሩስያ ጉዳይ ብቻ አይሳብም የደቡብ ሱዳን እና የሱማልያው ጉዳይ ገና  አቅጣጫቸው በአግባቡ ያልለየላቸው መሆኑ እና ኢትዮጵያ አሁንም ወሳኝ መሆኗን ማሰብ ይገባል።እዚህ ላይ የኤርትራ ዕድልም እራሱ የሚታየው የአዲስ አበባ ፊት እየታየ መሆኑ እውነታው ነው።እነኝህ ሁሉ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መረጋጋት እና ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረስ እንዳለበት ለማመን ሊቅ መሆን አይጠይቅም።

በኢትዮጵያ ኢህአዲግ የህዝቡን ስሜት እና የፖለቲካ ሳይንስ ተከትሎ ለለውጥ አለመዘጋጀቱ እና የጎሳ ፖለቲካውን ከሚገባው በላይ መወጠሩ ኢትዮጵያ አስፈሪ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያሰጋል።ይህንን ስጋት ማስወገድ ማለት ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ሚና የምትጫወተውን ግብፅን ብቻ ሳይሆን የቀይ ባህርንም የመቆጣጠር ዕድል መሆኑን ወዳጅም ጠላትም የሚረዳው ጉዳይ ነው።ጠላት ከመቼውም በበለጠ ሁኔታ ኢትዮጵያን በጎሳ ለማተራመስ ሲሰራ ወዳጅ ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ የበላይነቷን እንድትይዝ ይሰራል።ከእዚህ በተለየ ደግሞ  ባእዳን ጥቅማቸውን በማንኛውም መንገድ ከሚያስከብርላቸው ጋር ለመስራት ይተጋሉ።ጥያቄው ለኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል የሚፈጥረውን መንገድ መርጦ የሚሄድ መንግስት አላት ወይ? የሚል እና ተቃዋሚው ኃይልስ ምን እየሰራ ነው? የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው።

 ለኢትዮጵያ ያሏት እድሎች ሁለት ናቸው።አንድኛው-ኢህአዲግ እራሱ ለለውጥ ማዘጋጀት እና ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ዕድል እንድትጠቀም ''360 ዲግሪ የዞረ'' የፖሊሲ ለውጥ ማሳየት እና ቅድምያ ለሃገር ቢሰጥ ያለንበትን ታሪካዊ ዕድል ለመጠቀም መቻል ነው።ካለፉት የኢህአዲግ ተግባራት ተነስተን ይህ ለብዙዎቻችን ሕልም ነው።ኢህአዲግ ለሀገር ቅድምያ ባለመስጠት ዝናን ያተረፈ ነው።ይህ ካልሆነ ግን ጉዳዩ ያለው ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ነው ማለት ነው። የኢትዮጵያ የተቃውሞ ኃይላት እራሳቸውን በፍጥነት የሚያስተባብሩበት ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆኑን መረዳት ይቻላል።ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩ የሆነ ህብረት እና አዲስ አቀራረብ ይዘው ከሰሞኑ መገኘት እና ለልዕለ ሃያላኑንም ሆነ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስበን ዜጎች ሁሉ ከጊዜያዊ ሕብረት ይልቅ ፍፁም የሆነ አንድነት እና የለውጥ ስልት ሊያሳዩን ይገባቸዋል።ዓለም አቀፋውም ሆነ አካባቢያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚያመላክተው ይህንኑ ነው።ጊዜ ያለ አይመስልም።

ጉዳያችን
ሚያዝያ 16/2006 ዓም 

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።