ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 4, 2014

ብሔርን ወይንም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ብዙ ዕርቀት የማይሄዱባቸው ሶስት ምክንያቶች



በሀገራችን ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የመገናኛ ብዙሃን ከሃገር ቤት ውጭ  ይገኛሉ።እነኝህ የመገናኛ ብዙሃን የቴክኖሎጂ ዘመን ነውና ወደ ሀገር ቤት የሚደርሱባቸው በርካታ አማራጮች ሊኖራቸው ይችላል።እነኝህን የመገናኛ ብዙሃን ባብዛኛው በግልፅ የተቀመጠ ነው እና የኢድቶርያል ፖሊሲ ዓላማቸውን እና ግባቸውን መለየት ብዙም ከባድ አይደለም።

በእዚህ መሰረትም የመገናኛ ብዙሃኑን በሁለት ክፍል መክፈል ይቻላል።የመጀመርያዎቹ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱ ሲሆኑ የተቀሩት የመጡበትን ጎሳ ቋንቋ መሰረት አድርገው የተመሰረቱ ናቸው።ዛሬ ለማንሳት የምፈልገው ግን ብሔርን ወይንም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ የመገናኛ ብዙሃን ብዙ ዕርቀት የማይሄዱባቸው ሶስቱን ምክንያቶች ነው።

ምክንያት 1
የጎሰኛነት ስሜት እንደ 'ኩፍኝ' ነው ይለቃል የሃገራዊ ስሜት ግን የተዳፈነ ፍም ነው።


በአንድ የተወሰነ ርዕዮተ አለም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ በሰፈርተኝነት ላይ የተመሰረተ ሥራ የአንድ ሰሞን ግርግርታ ናቸው።የኩፍኝ በሽታ በትክክል ይመስላቸዋል።ኩፍኝ የአንድ ሰሞን በሽታ ነች።ካልታከመች አደገኛ ነች።ከታከመች ግን የትም አትደርስም።በዘመነ ደርግ ስለሶሻሊዝም ስህተት ለአንድ የቀበሌ ጥበቃ መናገር እስከሞት የሚያደርስ ፍርድ ሊያሰጥ ይችላል።በወቅቱ ገዳዩ ስለመግደሉ እርግጠኛ ነበር።ከአመታት በኃላ ኩፍኙ አልፉ ሲመለከተው ግን ስህተቱ ይታየዋል።የብሔር ስሜት እና መሰረቱ እርሱን ያደረገው ሚድያም ይሄው ነው።
ዛሬ እሞትለታለሁ ያለው የሰፈር ስሜት ነገ በኢትዮጵያዊነት እስኪማረክ ብዙ ይባልለታል።ያኩራራል።ያስደስታል።በሂደት ግን መማርያ ይሆናል።
የሃገራዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ግን ጥብቅ የሆነ ማኅበራዊ፣ስሜታዊ እና ዘመናዊ እሴቶችን ይዞ ከውስጥ እየፈነቀለ ጥላቻ ላይ በረዶ ይከልስበታል።እናም ሚድያ ዘለቄታዊውን እንጂ ጎሳዊ ስሜት ይዞ መሄድ አያዋጣውም።

ምክንያት 2 

ጎሰኘነት የጎሳውን ስሜት ለመኮርኮር ይጥራል።ሃገራዊ ስሜት ግን ዓለምን ይኮረኩራል።


በጎሳ ላይ የተመሰረተ ሚድያ ሁል ጊዜ እጁም፣እግሩም መላ ሰውነቱ የጎሳውን ውሎ፣ብሶት፣ትልቅነት ወዘተ አግንኖ ለማቅረብ ይጥራል።ስራው ሁሉ የጎሳውን ስሜት ለመኮርኮር ነው።ሃገራዊ ስሜትን የሚያንፀባርቅ ሚድያ ግን አቅርቦቱ ሁሉ ሃገሩን አልፎም አካባቢውን ከፍ ሲል ደግሞ ዓለምን ይኮረኩራል።የሚነሱት ጉዳዮች የሌሎችን ሃገራት ጥቅም እና ጉዳት ስለሚመለከት ትኩረት ይስባል።እርግጥ ነው የጎሳ ጥቅም የሌሎችን የሚነካባቸው ብዙ መንገዶች ይኖራሉ።በሀገራት ደረጃ ስናየው ግን ብሔራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረውን ቅድምያ የሚሰጡባቸው ብዙ መንገዶች አሉ።

ምክንያት 3
ጎሰኝነት ሲነሳ ብዙ አጃቢ አለው።ሃገራዊው ስሜት ግን ከመነሻው ይልቅ እየቆዩ የሚቀላቀሉት ይበልጣሉ።


የጎሰኝነት ስሜት ይዘው የሚነሱ ሚድያዎች መነሻቸው ላይ የጎሳቸውን ስሜት በእጅጉ ይኮረኩራሉ።ለእዚህም ምክንያቶች አሉት።እነርሱም የጎሳቸውን ኩራት በእጅጉ ከፍ ያደረጉ ተደርገው በመጀመርያ ላይ ይታያሉ።እየቆየ ግን እራሱን የተለየ አድርጎ ሲያስብ የነበረው ጎሳ እራሱን ለብቻው መነጠሉ ውበቱን ሳይሆን የጎደሉትን መሰረታዊ ዘመናዊ አስተሳሰቦች እየጎሉ ሲመጡ በመጀመርያ እጁን የሚያነሳበት እና የምቃወመው ሲያከብረው ወደነበረው ''የጎሳዬ'' ወዳለው 'ጎሰኛ' ሚድያ ይሆናል።ቀድሞ ነገር የብዙሃን መገናኛ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ጎሳ የሌለው ለሁሉም የሚያገለግል ማለት ነው።ጎሳውን የለየ ሚድያ እንዴት ብሎ ከጊዝያዊ ስኬት ባለፈ ውጤታማ ሊሆን ይችላል?

ባጠቃላይ የጎሰኝነት ስሜቶች እና ኃይሎች አንዴ በፓርቲ መልክ ሌላ ጊዜ በሚድያ መልክ ሲፈልጉ ደግሞ በንግድ ድርጅት መልክ ቢከሰቱም መጨረሻ አሸናፊው ኢትዮጵያዊነት ነው።ይህ ፉከራ አይደለም ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ከበቂ በላይ ናቸው።አምባገነንነት፣ፋሽዝም፣ናዚዝም መሰረታቸው ርዕዮተ ዓለም አይደለም ጎሰኝነት እና የእኔ ዘር ይበልጣል ነው።መነሻቸው ላይ የናዚው ሂትለርም ሆነ የፋሺሽቱ ሞሶሎኒ  ሺዎችን በንግግራቸው አስደምመዋል፣አስፈንጥዘዋል፣ለጎሳቸው ኩራት መሰል በርካታ ቁራጥራጮች  ወርውረዋል።ነገር ግን ይህ ሁሉ ሁካታ ከአምስት አመታት በላይ አልዘለቀም የእውነት ኃይሎች ተነሱ። አሸነፉት።አሳሳቢው የእውነት ኢትዮጵያዊነት ስሜትን ያነገቡቱ ምን ያህል ፀንተው ይቆማሉ? ነው።ሁሉም ሊፀና፣ሊቆምለት እና ሊያግዝ የሚገባውም ኢትዮጵያዊነትን ያነገቡትን ሚድያዎች ነው።ይህ እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያዊነት አሸንፎ ይወጣል።አሁንም ተረት አይደለም።
 
ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

የካቲት 25/2006 ዓም

No comments: