ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, September 1, 2013

ሕጉ ለሕግ አክባሪው ከለላ ካልሰጠ ሕግ አለማክበር ሆይ ምንኛ ታላቅ ነሽ! (አጭር ማስታወሻ)


 የሕግ ከለላን እና በሕገመንግሥቱ የተቀመጠውን ሕግ ተማምነው የሰላማዊ ሰልፍ የጠየቁ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለእሁድ ነሐሴ 26 ሰልፍ በዝግጅት ላይ ሳሉ ቅዳሜ ነሐሴ 25 ምሽት  በፅህፈት ቤታቸው ላይ በተደረገው ድንገተኛ የፌድራል ፖሊስ የማሸበር ተግባር ተደብድበዋል፣ተሰድበዋል ግማሾቹ ለከፍተኛ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል።

 የተቀመጠው ሕግ የሚሰራው የአይን ቀለም እና ምላስ እየለየ መሆኑ ተነግሯቸዋል።በድብደባው ወቅት ተሰድበዋል፣ተረግጠዋል። በኢትዮጵያ ሕግ ስር በህጋዊነት የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ቀርቶ የንግድ ፍቃድ አውጥታ የምትሰራ ለትንሿ ኪዮስክም ተገቢ ክብር መስጠትለታደለ መንግስት የሚከውናት ትንሿ ተግባር ነበረች። ማክበር ደግሞ ለመከበር ይጠቅማል። የወያኔ ታጣቂዎች ግን ከእነርሱ አስተሳሰብ በተለየ የሚያስበውን ግለሰብም ሆነ ድርጅት በጠላትነት ፈርጀው ሃገሩ የእነርሱ የአምባገነንነት ላንቃ ማላቀቅያ ሲያደርጉት ማየት አለመታደል ነው።አንዳንዶች እጅግ ከበዛ ፍርሃታቸው እና ለስርዓቱ ካላቸው አፈር የላሰ ታማኝነት የተነሳ በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ የተፈፀመው የማሸበር ተግባር ''እንዳስደሰታቸው ሲናገሩ'' አፋቸውን ትንሽም ወለም አይላቸውም። የሰማያዊ ፓርቲ የመሰሉ ፍትህ፣ስርዓት እና የሕግ ልዕልና ይኑር የሚሉ ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች የሚታገሉት ለእነዚህ የስርዓቱ ታማኞችም ጭምር ለነገ ዋስትና እየታገሉ መሆናቸውን አለመረዳታቸው የግንዛቤ ውሱንነትን ያመላክታል።

እርግጥ ነው ይህ ክስተት ላለፉት 22 አመታት ሲከናወን የነበረ መሆኑ ዛሬ እንደ አዲስ ሊወሳ ላይችል ይችላል።ጉዳዩን ለማውገዝም ሆነ ወያኔ የሚማርበትን ሁነኛ መንገድ መፍጠር የግድ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆን ወይንም ፓርቲውን በቅርብ ማወቅ አይጠይቅም።የእዚህ አይነቱን  የእብሪት ተግባር  የመግታት ተግባር የእዚህ ትውልድ ዕዳ ለመሆኑ ግን ቅንጣት  ታክል መጠራጠር አይገባም።

የሃገራችሁ መፃኢ ዕድል አሳስቧችሁ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆናችሁም ሆናችሁ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የታተራችሁ ሁሉ ክብር ሊቸራችሁ ይገባል።ዘመን ስም ሊለጥፍ ይችላል። በፋሽሽት ጣልያን ዘመን ለኢትዮጵያ ነፃነት በዱር በገደሉ የሚጋዳሉ አርበኞችን ፋሺሽት ''ወንበዴዎች'' ይባሉ ነበር።በዘመነ ደርግ ዲሞክራሲ ያሉ ''የኢምፐራሊዝም'' አቀንቃኞች ይባሉ ነበር።እናንተም  ለሕግ፣ለሞራል እና ለሥርዓት እንደምትገዙ በመግለፅ ጥያቄያችሁን አቀረባችሁ።መልሱ ግን በግፍ መደብደብ ሆነ።ካለስማችሁ ስም ተሰጣችሁ። የእዚህ ጊዜ ነው ታድያ ሕጉ ለሕግ አክባሪው ከለላ ካልሰጠ ሕግ አለማክበር ሆይ  ምንኛ ታላቅ ነሽ! ማለት ተገቢ የሚሆነው።





ጉዳያችን GUDAYACHNgetachewb221@gmail.com

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።