ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, May 28, 2013

ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግንቦት 20 ካለፈው ይልቅ መጪውን የሚፈሩበት ጊዜ ነው

ግንቦት 20፣1983 ዓም ታላቁ ቤተመንግስት በር 
ዛሬ ግንቦት 20 ነው።ግንቦት 20 የኢትዮጵያ የፖለቲካ መዘውር የተዘወረበት ለመሆኑ አሌ አይባልም። ዕለቱ እንደ አቶ ሃይለማርያም የመጀመርያ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ እንዳደረጉት ንግግር '' ኢትዮጵያ ልትበታተን ስትል የዳነችበት ቀን'' ነው ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ግንቦት 20 ካለፈው ይልቅ መጪውን የሚፈሩበት ጊዜ ነው።ይህንን ሁለተኛውን ሃሳብ እኔም እጋራዋለሁ። ካለፈው ይልቅ መጪው ይቀርበናል።ያለፈውማ አለፈ።መጪው ግን ቢዘገይም ቢፈጥንም አይቀርም።እና ግንቦት 20 ካለፈው ይልቅ ለመጪዋ ኢትዮጵያ እንዴት አስጊ ያደርገዋል። ይህንን ለማብራራት ግንቦት 20 እንደ ሀገር ለኢትዮጵያ ይዞት የመጣውን በጥቂቱም መጥቀስ ይፈልጋል።ስለተሰራው የመንገድ እርዝመት፣ህንፃ፣ወዘተ ማተት ይቻላል።እርግጥ ነው መንገድ ተስርቷል።ህንፃ ተገንብቷል።ከተሞች ሰፍተዋል።ይህ ሁሉ  ግን መጪውን አስፈሪ ጊዜ ለሀገር ከመተው አልገታውም።

መጪውን አስፈሪ የሚያደርገው የግንቦት 20 ውጤቶች ምን ምን ናቸው? 

እንድሜ ለግንቦት 20 ብዬ ብጀምርስ-

  • እድሜ ለግንቦት 20 ዛሬ ኢትዮጵያ በአለም ታይቶ በማይታወቅ መልክ በቁጥር ተከልላ ክልሎች ስለ ድንበሮቻቸው ሲደራደሩ አንዳንዴም ሲጋጩ ለማየት በቅተናል።ምሳሌ የአፋር እና ትግራይ፣የሱማሌ እና ኦሮሞ፣የአማራ እና አፋር ወዘተ መጥቀስ ይቻላል።
  • እድሜ ለግንቦት 20 አንድሰው ከአንዱ የሃገሪቱ ክልል ተነስቶ እንበል ደቡብ ወይንም ጅጅጋ  ገብቶ መሬት ገዝቶ ልረስ ወይንም ልነግድ  ቢል እርሱ ከመምጣቱ በፊት ከ 60 እና 70 አመት በፊት የሰፈሩቱ ከጉርዳፈርዳ፣ጋምቤላ፣ጅጅጋ እና አሶሳ ካለምንም ካሳ ሲባረሩ ያያል እና መጪው እያስፈራው አይሞክረውም።
  • እድሜ ለግንቦት 20 ወላጆች ልጆቻቸውን በፈለጉት ቋንቋ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ በታሪካዊ አጋጣሚ የሚኖሩበት ክልል ቋንቋ ውጭ እንዳይስተምሩ ታግደዋል።ለምሳሌ ኦሮምኛ ተናጋሪ ልጁ በአማርኛ እንዲማር ቢፈልግ ግን በኦሮምያ ክልል ቢኖር አማርኛ ወደምነገርበት ክልል መሄድ ብቸኛ አማራጩ ነው።በምዕራቡ አለም የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ግን ልጁን በሀገሩ ቋንቋ እንዲያስተምር ባህሉን እንዲጠብቅ ድጋፍ ይደረግለታል።
  • እድሜ ለግንቦት 20 ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና የባህር ኃይሏን በትና  30 እና 40 ኪሎሜትር እርቀት የባህሩ ማዕበል ሲማታ እየተሰማ ከ85ሚልዮን በላይ ሕዝብ ወደብ አጥቶ የጅቡቲን እና የሱዳንን ወደቦች በከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍል ተወስኖበታል፣
  • እድሜ ለግንቦት 20  ጦርነት ቆመ በተባለበት ጊዜ በአዲስ አበባ ብቻ ከ 100ሺህ በላይ ''ጎዳና ቤቴ'' ያሉ ሕፃናት መንገድ ላይ ፈሰው ኃላፊነት የሚወስድ መንግስት አጥተው ለማየት የበቃነው በግንቦት 20 ፍሬ ነው። (በቀድሞው መንግስት የተመሰረተው የሕፃናት አንባ እንዴት በአሁኑ መንግስት እንደፈረሰ ይህንን ሊንክ ከፍተው ቪድዮውን ይመልከቱ (http://gudayachn.blogspot.no/2013/05/main-play-list-on-home-page-playlist.html)፣
  • እድሜ ለግንቦት 20 ከሃያ ሁለት አመት በፊት ''የጫት ቤት'' ብሎ በር ላይ መለጠፍ የምያሳፍርባት አዲስ አበባ ዛሬ ጫት በየዘርፉ ''የበለጩ ፣የባህርዳር፣ የወልሶ ጫት ቤት'' ብቻ ተብሎ ሳይሆን የሚለጠፈው ''ጫት እናስቅማለን፣ እንፈርሻለን'' ተብሎ የተፃፈባቸው ባብዛኛው ትምህርት ቤቶች የሚገኙበትን ቦታ ፈልገው የሚከፈቱ የጫት ቤቶች በዝተው ለመታየት በቅተዋል። ምን ይህ ብቻ ዩንቨርስቲዎቻችን በየዶርሙ ጫት ሸጉጠው ሲገቡ- ሲ ቃምባቸው ደጉ መንግስታችን በዝምታ አልፎ ትውልዱን ጫት ቃሚ አድርጎታል። 
  • አድሜ ለ ግንቦት 20 ምሳ ሰዓት ላይ ከቢሮ ወጥተው ጫት ቅመው የሚመለሱ የባንክ ሰራተኞች፣መሀንዲሶች ወዘተ አፍርቷል ግንቦት 20።ከደንበል ህንፃ ጀርባ የሚገኙ የመቃምያ ቦታዎችን ብንመለከት በምሳ ሰዓት ደንበል ህንፃ የሚሰሩ ምሁራን ዩንቨርስቲ ሳሉ በተፈቀደላቸው የመቃም መሰረት ሥራ ከያዙ በኃላም ለመላቀቅ ትቸግረው ይታያል።እረ  እንዲያውም በሥራ ሰዓት ሾለክ ብለው የሚቅሙ ሰራተኞች መኖራቸውን የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እማኝ ነው። እድሜ ለግንቦት 20።
  • እድሜ ለግንቦት 20 ወላጅ አልባ ሕፃናት ጎዳና እንዳይወጡ በሕዝቡ የሚደገፍ እንደ ሕፃናት አምባ መስርቶ ከማሳደግ ይልቅ ለአንድ ሕፃን እስከ 25000 ዶላር መንግስት እየተቀበለ በጉዲፈቻ ስም ለአሜሪካ እና አውሮፓ የተቸበቸቡት እና ብዙዎች በህሊና ስቃይ እና የማንንነት ጥያቄ እንዲሰቃዩ የተደረጉት በግንቦት 20 ፍሬ ነው (ሰኔ 25/2012 እአአቆጣጠር  በቢቢሲ ድህረ ገፅ ላይ በወጣ አንድ ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያ በአመት 5ሺህ በላይ ሕፃናት በማደጎነት ወደ አሜሪካ  ብቻ እንደሚሄዱ  እና አሜሪካ ከዓለም ላይ በማደጎነት ከምትወስደው ሕፃናት ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ከ አምስቱ አንዱ እንደሆኑይገልፃል።(http://www.bbc.co.uk/news/world-africa-18506474)
  • እድሜ ለግንቦት 20 ሴት እህቶቻችን ተስፋ ቆርጠው ለአረብ ሀገር ባርነት  በአስርሺዎች የተጋዙት በሄዱበት ሀገርም ስበልደሉ የሚሰማቸው አጥተው አሳር ፍዳቸውን የሚያዩት ከግንቦት 20 ፍሬ ወዲህ ነው።
  • እድሜ ለግንቦት 20 ''የኤርትራ ጥያቄን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት የሚቻለው የ ሻብያን ሃሳብ በመቀበል ነው'' ብለው ስያግባቡን የነበሩት  አቶ መለስ- ጦርነቱ አበቃ ከተባለ ከ ሰባት አመታት በኋላ ለዳግም እልቂት ''ድንበር'' በሚል ሰበብ ዳግም የኢኮኖሚ ፀባቸውን ወደ ወታደራዊ ግጭት ቀይረው በአስር ሺዎች የረገፉት በ ግንቦት ሃያ ውጤት ነው፣
  • እድሜ ለግንቦት 20 ስደት ቀድሞ የነበረ ቢሆንም በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ በባህር፣በእግር ወዘተ ወጣቱ ከሀገር የሚወጣው ከግንቦት 20 ፍሬ ወዲህ ነው (ወደየመን በጀልባ ተሳፍረው ከገቡት ስደተኞች ከ 70%በላይ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን በዘንድሮው ዘገባው መጥቀሱን ልብ በሉ) ፣
  • እድሜ ለግንቦት 20 ወጣቶች ተምረው በእውቀታቸው ሀገርንም መጥቀም ሲገባቸው፣የስራ ዕድል የሚያገኙበት ወይንም  ስነልቦናቸውን የሚጠብቅ ግን ለፈጠራ የሚያዘጋጅ የስራ መስክ ከመፍጠር ይልቅ በምረቃቸው ጊዜ (የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ  2004ዓም ምረቃ ላይ አቶ ጁነዲን ለተማሪዎቹ እንደተናገሩት)ከዩንቨርስቲ ሲወጡ  የኮብል ስቶን ሥራን መስራት እንደሚገባ የተነገራቸው በግንቦት 20 ውጤት ነው። 
  • እድሜ ለግንቦት 20 በሚድያውስ ቢሆን (ጎረቤት ኬንያን ለማነፃፀርያ እንጠቀም) ኬንያ የህዝብ ብዛቷ 30 ሚልዮን ሲሆን እኛ 85 ሚልዮን መሆኑን እናስታውስ እና ኬንያ በይዘታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው የመንግስት እጅ ያልተጫናቸው 8 የቴሌቭዥን ጣቢያ፣ 38 ራድዮ ጣብያዎች፣ ከእሩብ ሚልዮን በላይ አንባቢ ያላቸው በየቀኑ የሚታተሙ 4 ጋዜጦች (http://www.pressreference.com/Gu-Ku/Kenya.html#b) ሲኖሩ ሃሳብን የመግለፅ መብት እና በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ የመወያየት ነፃነት ከእኛ ጋር ሊወዳደር የማይችል መሆኑን ስናስብ እና ጋዜጠኞች መንግስትን ወቀሱ ተብለው በአሸባሪነት ዘብጥያ መውረዳቸውን ስናስብ እድሜ ለግንቦት 20 እንላለን።
  • እድሜ ለ ግንቦት 20 ጋና ነፃነቷን ስታገኝ የገነባነው ስታድዮም ዛሬ ጋና ከነፃነት አልፋ እስከ መቶ ሺሕዝብ የሚይዝ ስታድዮም ስትገነባ እኛ አሁንም አንድ ለእናቱ በሆነ ስታድዮም መገኘታችን የግንቦት 20 ውጤት ነው።እርግጥ ነው በዛሬው የግንቦት 20 በዓል የስፖርት አካዳሚ ምረቃ በአል እየተከበረ ነው። ስታድዮምስ ?
  • እድሜ ለግንቦት 20 ቀድሞ ጉቦ የሚለው ቃል ሲነሳ ስለ 20 እና 30 ብር ጉቦ እናስብ ነበር። ዛሬ ጉቦ፣ሙስና እና ዝርፍያ ማለት አድገው ተመንድገው  ዝርፍያ ማለት የብሔራዊ ባንክን የወርቅ ክምችት በወርቅ መሰል ነገር መቀየር ሲሆን ጉቦ ማለት ደግሞ የሀገር መሬት እና ውሃን  ለሕንድ እና ለአረብ በርካሽ መቸብቸብ ፣ በባለስልጣናት ቤት እንደባንክ ቤት በኢይሮ ብሉ በዶላር ቢሉ በፈለጉት የገንዘብ አይነት ከቤት ማስቀመጥ ማለት ነው (በቅርቡ የግምሩክ ባለስልጣናት ቤት  ተገኘ የተባለውን ብር ያስታውሱ)።

ይህንን ሁሉ ስናስብ ነው እንግዲህ ግንቦት 20 ካለፈው ይልቅ መጪውን የሚያስፈራ የሚያደርግብኝ።ከሁሉ የከፋው ግን መንግስት ስለሰራሁት መንገድ እና ድልድይ ስታመሰግኑኝ መስማት ብቻ ነው የምፈልገው ከማለቱም በላይ መሰረታዊ ስህተቶችን ''የጨለምተኞች አመለካከት'፣ የአመለካከት ችግር'' እያለ ማጣጣሉን መቀጠሉ ነው አሳዛኙ።

አበቃሁ 
ጌታቸው 
ኦስሎ 

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።