ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, January 26, 2013

ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው-ለ ብሔራዊ ቡድናችን ፣ለ አሰልጣኞች እና ለደጋፊዎች ሁሉ

ፎቶ ከ ድሬ ዩቱብ (ለ ናይጀርያው ግጥምያ ዝግጅት ላይ)
 
 
ትናንት አርብ ጥር 17/ 2005 ዓም ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ደቡብ አፍሪካ የተላለፈው ኢትዮጵያ እና ቡኪናፋሶ እግር ኳስ ውድድር ኳስን መሰረታዊ ባህሪ በያዘ መልኩ ማለትም ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ አንዱን መርጦ አብቅቷል። አዎን ኢትዮጵያ በኩል አራት ጎሎች ተቆጥረዋል። ጫወታው እንዳበቃ በመጀመርያ በጣም ተናደድኩ ትንሽ ቆይቼ ነገሩ አለመሞቱ ግን ቡድኑ ሞራል ምን ያህል ይሆን? የሚለው ብቻ አሳሰበኝ።ዛሬ ቅዳሜ ጫወታውን ደግሜ አየሁት።በ እውነት ትናንት ያልታዩኝ የተጫዋቾቻችን ድንቅ ጥበብ ታየኝ።ሰው አንድን ነገር ለመመልከት የረጋ ልቦና ይሻል የሚባለው ልክ ነው።ዛሬ ከስሜት ውጭ ሆኘ ስመከት ቡድናችንን የሚያስደንቁ ጥበቦቹ ታዩኝ።እናም የሚከበር ቡድን ግን አኛ ተመልካቾች ልናከብረው እና ልናደንቀው የሚገባ ነው ብዬ አሰብኩ።
አንድ ወቅት አስራዎች አመታት በፊት ግብፅ ውስጥ ብሔራዊ ቡድናችን (ለማጣርያ ይመስለኛል)ሲጫወት ቡድኑን ለማዋከብ የነበረው ተመልካች ዘዴ በጣም መጮህ እና እዚህ በፊት ሰማንያ አና ዘጠና ሕዝብ የተሞላ ስታድዮም ውስጥ ተጫውቶ የማያውቀውን ተጫዋች ማዋከብ ነበር። በወቅቱ ቡድናችን አለም አቀፍ ጫወታ ተሞክሮ ስሌለው እና ሰላሳ ሕዝብ የሚይዝ አዲስ አበባውን ስታድዮም ብቻ ስለሚያውቅ ትልቅ ችግር ፈጥሮ ነበር። አሁን አቅም ተፈጥሮ ጫወታው ቴክኒክ ሁሉ ጥሮ መስመር ላይ ነው ያለው። የተሞከሩት ጎል ሙከራዎች ዕድል ጉዳይ እንጂ ምርጥ ተጫዋቾች እንዳሉን ለመረዳት አይናችንን የሚከፍቱ ናቸው።አሁን የቀረን አንዲት ነገር ነች። ጀግንነት፣እራስን ማወቅ፣ካለምንም ጉራ ታላቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ማወቅ፣ይህንንም ለቡድኑ መንገር።ሽንፈት የሚጀምረው እራስን ዝቅ አድርጎ ማየት ሲጀመር ነው።ቡክናፋሶች ጎል ዕድል ቢያገኙም፣በ ጫወታ ቢገዳደሩንም፣ አሁንም የማሸነፍ እድላችን እጃችን ውስጥ መሆኗን ማወቅ አለብን። መሸነፍ፣ፈተና፣ተስፋ መቁረጥ አንዳንዴ ተደጋግመው የተጫኑ የሚመስሉበት ጊዜ አለ። እዚህ ላይ ነው ጀግና የሚያስፈልገው። ''ቁርጥ ቀን ባይመጣ ሁሉም ጀግና ነበር'' የሚባለው እዚህ ቀን ነው። ቡድናችን አሰልጣኞቻችን ሁሉ በአንድ መንፈስ ቀጣዩን ጫወታ እንደሚያሸንፉ ሙሉ ልብ እራሳቸውን ከማወቅ እና ከማክበር ጋር ይጫወቱ ይመኑ ታምር ይሰራሉ።

እዚህ ላይ በቡድናችን የሞራል መጠበቅ ላይ እክል ፈጥረዋል የተባሉ ወደፊት ጥብቅ ምርመራ የሚፈልጉ እና በቀላሉ የማይታዩ ጉዳዮች እንደነበሩ ይወራሉ። ይህንን በተለይ አስልጣኝ ሰውነትም ሆኑ ምክትላቸው ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰሩ ለ ፖለቲካው አካላት ም ሆነ ለሕዝቡ በድፍረት እንዲነግሩልን እንጠብቃለን። በ እዚህ ዘመን ''የተሰወረ የማይታይ ያልታወቅ የማይገልጥ'' የለምና። ለሁሉም ግን አሁን መደረግ ያለበት  ቢያንስ ቀጣዩ ጫወታዎች እስከሚጠናቀቁ በ ትዕግስት የ ቡድኑንም ሆነ የደጋፊውን ህብረት እንዲጠበቅ ማድረግ ይመስለኛል።

ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም ዕድል ወይንም ትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል።የዓለማችን ጀግኖች ተሸነፉ ሲባሉ እንደገና ተነስተው ስለሚያሸንፉ ያለፈውን ሽንፈታቸው ከቶ ማን ሊያስበው ይቻላል? እንግሊዝን እስኪ አለም ዋንጫ ላይ የሚደርስባትን እንመልከት።እንዲያ ድንቅ ክለቦች ያላት ሀገር በዓለም ዋንጫ ላይ ግማሽ መድረስ ሲያቅታት እንግሊዝ ሕዝብ እና መንግስት ሰቀቀን የማይሆን ይመስለናል ? ግን እንግሊዞች ኳስ ስለማይችሉ ነው የተሸነፉት? አይደለም። ኳስ እንዲህ ስለሆነች ነው። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጫወታ ዛሬ አለፍ አለፍ እያልኩ ቡክናፋሶ ጋር ያደረገውን ጫወታ ስመለከት እጅግ ድንቅ ተጫዋቾች እንዳሉን ግን እኛ ልናከብራቸው፣ልናደንቃቸው፣ ታላቅ ችሎታ እንዳላቸው አንዳንድ ቴክኒካዊ ስራዎችን እያስተካከሉ እንዲሄዱ እራሳቸውን ዝቅ እንዳያደርጉ መንገር ባለዑያዎች ብቻ እንደሚገባ አመንኩ። ይህ ደግሞ ለሽንገላ ሳይሆን ቀድሞ የነበረው ''እኛ ኳስ አይሆንልንም'' የሚባልበት ጊዜ ላይ ላለመሆናችን ችሎታቸውን ልዩ አቀራረብ ያሳዩን ተጫዋቾች ምስክር ናቸው። ዛሬ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃዋ አለም አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያንም ያስደነቀን ጉዳይ ነው። ወደ ኋላ ፈፅሞ መመለስ የለም!

በመጪው ማክሰኞ ናይጄርያ ጋር በሚኖረው ውድድር ተአምር የመስራት ብቃቱም ሆነ አቅሙ አላችሁ።በ አንድ በኩል ናይጀርያ በትናንትናው ቡክናፋሶ ጋር በተደረገው ጫወታ ቡድናችንን ዝቅ አድርጎ የማየት ሁኔታ ሊኖር እንድሚችል ይገመታል።ይህ ጥሩ ዕድል ነው።

እርግጥም ቡክናፋሶ ጋር የሆነ አምላክ እኛ ጋርም አለ። ናይጄርያ ጋር ያለ አምላክ እኛ ጋርም አለ። ቀጣዩን ናይጄርያ ጋርም ሆነ ቀጥለው በሚከፈቱት ዕድሎች ቡድናችን እንዲያሸንፍ እኛ ተመልካቾች የምናደርገው ሁለት ነገር ነው። አንድ ስታድዮም ተገኝቶ መደገፍ ሁለተኛው እና ዋናው ማንም ችላ ሊለው ወይንም ሊረሳው የማይገባው ከልብ የሆነ ቢያንስ ጥቂት ደቂቃዎች ልመና ወደ እግዚአብሔር ማቅረብን ነው። ያኔ ሁሉም ግዴታውን ተወጣ ማለት ይቻላል።የ ኢትዮጵያን ቡድን ያወደሱ ብእሮች እንደገና ይቀረፃሉ።ዋልያዎች በርቱ!

ጀግንነት ፈፅሞ አለመሸነፍ አይደለም። ተሸንፎ መነሳት ነው። ጀግናን ጀግና የሚያሰኘው ፈፅሞ የማይሸነፍ ምትሃታዊ ፍጥረት ስለሆነ አይደለም ዕድል ወይንም ትንሽ ስህተት አልያም ችላ ብሎት ጀግና የመጀመርያ ሽንፈት ይሸነፋል። ሁለተኛ እና ሶስተኛ ላይ ግን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን የሚያርበደብድ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ዘላለም ትኑር!

ጌታቸው  

ኦስሎ

No comments: