ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, June 7, 2012

''የዛሬ 21 ዓመት እንዲህ ነበር ዛሬ ግን ... ሲባል መስማት ይህ ትውልድ ከምር ሰልችቶታል።'' ትውልዱ ''የይሁዳ አንበሳ ለ ክርስቶስ የተሰጠ ስም ነው።''ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ስላሴ

ኢቲቪ አሁንም ድረስ ዜና አንባቢው ጀርባ ያለው ማስታወቅያ ግንቦት ሃያ የሚለው መሆኑ ምን ያህል ችክ ያለ ፕሮፓጋንዳ መጠመዱን ያሳያል- ኢህአዲግ።ጀግና ከተጠራ በእርስ በርስ ጦርነት ከ ወንድሞቹ ጋር የተዋጋው ሰራዊት ይነገርባታል።ልማት ከተባለ ከ 21 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ያልነበረች ይመስል'' ከ ግንቦት እስከ ግንቦት የዛሬ 21 ዓመት እንዲህ ነበር ዛሬ ግን ... እየተባለ መስማት ይህ ትውልድ ከምር ሰልችቶታል።
ሃገራችን የታሪክ ዳራ፣ስር፣መነሻ ያላት ሃገር ነች።በ ሃያ አንድ አመት መወሰን ''ከ አፍንጫ እስከ አፍ'' የማሰብ ድንክዬ አስተሳሰብ ነው። አዲሱ ትውልድን ዛሬ ማታለል አይቻልም።ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነውና።
ልዑል ኤርምያስ ሳህለስላሴ የ አጼ ሃይለስላሴ የ ልጅ ልጅ በ አሜሪካው ኮንግረስ መጻህፍት ቤት ተገኝተው አድርገውት የነበረውን ንግግር ለ አሁኑ ትውልድ ከ 21  አመት በላይ ስለነበረችው ሃገራችን ታሪክ በሚገባ እንዲረዳ እንደሚያደርገው እገነዘባለሁ። በእዚህ አጋጣሚ አንዳንዶቻችን የምናውቃቸውን ታሪኮች አዲሱ ትውልድ በ 21 ዓመት ታሪክ ትረካ ስለተጎዳ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ታሪክን  ማስተላለፍ መቻል ሃላፊነት መሆኑን ልብ እንድትሉልኝ እጠይቃለሁ።
የጉዳያችን ብሎግ ጦማሪ የንጉሳዊ አስተዳደር ናፋቂ ባይሆንም እንደ እዚህ አይነት ታሪኮች (የቀደመው የ ሃገራችን የ ዘውድ ታሪክ) ከህብረተሰቡ ታሪካዊ እና ሞራላዊ ጉዳዮች ጋር የነበረው ተዛምዶ በተመለከተ  ከ ሶስት አቅጣጫዎች ሲታፈኑ ታዝቧል።
1/ በንጉሱ ስርዓት ላይ በተነሳው አብዮት የተሳተፉ የ ''ያ ትውልድ'' አባላት

 በወቅቱ የ ንጉሱ ስርዓት የነበሩበት የ ብዝበዛ አይነት፣ግራ የተጋባ አካሂያድ እና ዓለም ዓቀፋዊ ክስተቶች ሁኔታዎችን ከሚገባው በላይ ቢያፋጥኑትም ታሪክ ግን ያውም ከ ሶስት ሺህ ዓመት በላይ የ ኢትዮጵያ አካል የነበረው የዘውድ ስርዓትን ቢያንስ በቅርስነት እንዳይወሳ መጣር ተገቢ አለመሆኑን ማንም አይስተውም።ይህ ግን በ ያ ትውልድ አባላት እና ተዋናይ ዘንድ 'ክብድ' ሲላቸው ይታያል::
2/  የ ደርግ ስርዓት


 በ 1953ዓም በ እነ መንግስቱ ንዋይ ተነስቶ የነበረው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ'' የሃገሬ ጉዳይ በጣም ስላሳሰበኝ ጻፍኩት'' ያሉት የ' ፍቅር እስከ መቃብር' መጽሃፍ ደራሲ እና ዲፕሎማት ሃዲስ አለማየሁ ''ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?'' በሚለው መጽሃፋቸው ላይ (መጽሃፉ የተጻፈው ገና የመጀመርያው የ ኢትዮጵያ አብዮት ሳይካሄድ ነበር) የደርግ መንግስት ሳይመጣ ሃገራችን ''ያሉዋት አማራጮች ሁለት ናቸው''  ።ብለዋል እነርሱም'' የ ምስራቁ አይነት አምባገነን መንግስት አልያም የ ምዕራቡ አይነት የ ንጉሳዊ ዲሞክራሲ'' መሆናቸውን ካወሱ በኋላ'' የ አምባገነን መንግስት ከመጣ አያምጣው እንጂ የህዝቡን ሃብት ለ ጆሮ ጠቢ ያባክናል፣የሃገሩን ሃብት ከልማት ይልቅ ለእርስ በርስ ውግያ ያውለዋል፣ስራው ሁሉ ስልጣን ማስጠበቅ ስለሚሆን ሃገራችን በ ዘር ፖለቲካ እንዳትገባ ያሰጋታል።ነገር ግን የ አምባገነን መንግስት በየትኛውም አለም እንደታየው ካለ ውጊያ ስልጣን ሊለቅ አይችልም ''ብለው ያስቀምጣሉ።
ደራሲ እና ዲፕሎማት ሃዲስ ዓለማየሁ ''ከሃገራችን ታሪካዊ ክስተት አንጻር የሚያስፈልጋት የመንግስት አስተዳደር ዘውዱ ለይስሙላ እንደ ሰንደቅ ዓላማ እና የ ሃገሪቱ አንድነት ተምሳሌነት ብቻ እንዲኖር አስተዳደሩ ግን በ እንግሊዝ እና በ ብዙ የ አውሮፓ ሃገራት እንዳለው ትክክለኛ ዲሞራስያዊ ምርጫ እያደረገ የምክር ቤቱንም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲመርጥ ቢደረግ ይበጃል።እዚህ ላይም የህግ ማውጣቱን እና የመቆጣጠር ስራ የ ምክር ቤቱ ሆኖ ዘውዱ የቀረበለትን ማጽደቅ ብቻ ይሆናል ስራው።''የ ዘውዱን አስፈላጊነት ሃዲስ አለማየሁ ሲያስገነዝቡ'' ኢትዮዽያ ከ ክርስቶስ ልደት በፊት በታሪክ፣በእምነት እና የ አንድነት ተምሳሌት ዘውድ ወርውራ ከጣለች ትልቅ የታሪክ እና የ ህልውና ቀውስ ውስጥ እንደምትገባ'' በማሳሰብ በወቅቱ የ ማኦኢዝምም ሆነ የ ራሻን አስተሳሰብ ይዞ የተነሳውን ትውልድ ሞግተዋል።
ያሉት አልቀረም ደርግም በተነሳ በ ቀናት ውስጥ ስልሳዎቹን የ ሃገሪቱን አሻራዎች ያለፍርድ ገደለ።በ እዚህ ወቅት የተገደሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮዽያ በ አካል ነው የተገደለችው። ከሞቱት ውስጥ የ ኢንዱስትሪውን ዕቅድ የያዘ አለ፣የሃገሪቱን የ እርሻ መንገድ ሲተልም የነበረ አለ፣ የባህር ሃይልን፣የምድር ጦርን ሚስጥር እንደያዘ እንደዋዛ የቀረ አለ። ያን ጊዜ የ ኢትዮዽያ ጠላቶች እንዴት ጮቤ እረግጠው ይሆን? እንደ ሃገር የሚፈርዋት ሁሉ የፈሩት ፋይል በ ጥይት አረር ዝም ሲልላቸው። ከ እዛማ ምን አለ 'ለ ሃገሩ እንግዳ ለ ህዝቡ ባዳ' እንዲሉ ደርግ እንዳዲስ ታሪክ ሊጀምር ተነሳ
3/  የ ኢህአዲግ መንግስት

ኢህአዲግ ገና በዱር እያለ ከሚያስተላልፈው የራድዮ ፕሮግራም ውስጥ የኢትዮዽያን  ያለፉ ታሪኮች ማጥቆር አንዱ አላማው ነበር። አሜሪካን ሃገር' በዘር የሚከፋፍል ፖለቲካ አንፈልግም' ብለው በደርግ ዘመን ይቃወሙ የነበሩትን እነ ተፈራ ዋልዋ' የ ነፍጠኛው እና ያለፉት ስርዓቶች ናፋቂዎች' እያሉ ስም ይለጥፉላቸው ነበር።ይህ ብቻ አይደለም ኢህአዲግ ስልጣን ከያዘ በኋላ የ አጼ ሃይለስላሴን አስከሬን ሲወጣ ''በ አለም ዙርያ ያሉ አድናቂዎቻቸውን ጠርተን በክብር የቀብር ስነስርዓት ይከናወን ይህ ለ ሃገራችን ትልቅ ዲፕሎማሲ ነው ኢህአዲግም ያስከብረዋል እንጂ አያስነቅፈውም'' ተብሎ በተደጋጋሚ ሲነገር  ''ንጉሱ የሚቀበሩት ከ ንግስና መውረዳቸው በደርግ ከተነገረ በኋላ ስለሆነ አሁን እንደ ተራ ሰው ነው የሚታዩት'' እንደ ኢህአዲጉ አውራ አነጋገር ተብሎ ከመንግስት ባለስልጣን  አንድም ዝር ሳይል ተከወነ። አሁንም ግን በሚገባ ክብር ባለመከወኑ ወደፊት ቀን ይጠብቃል እንጂ በክብር ይከወናል የሚሉትን ሳንዘነጋ።የ እዚህ ብሎግ ጸሃፊ በወቅቱ ስለ እዚሁ የ ኢህአዲግ በ አስከሬን ላይ ሳይቀር ለያዘው ቂም'' የ ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ'' ፕሮግራም ከ አዲስ አበባ በዘገበው ዘገባ ላይ በተሰነዘረው አስተያየት ''ዲፕሎማሲ ያልገባው የ ንጉሱን ለ ኢትዮዽያ መልካም ገጽታ ያላቸውን ክብር ያላገናዘበ  መንግስት'' ተብሎ መቅረቡን ያስታውሳል።ይህ ብቻ አይደለም በቅርቡ በ አፍሪካ ህብረት አዲሱ ህንጻ ላይ ብዙ የ አፍሪካ ምሁራን ለምን የ አጼ ሃይለስላሴ ሃውልት እንዲሰራ ኢትዮዽያ አልጠየቀችም ሲባሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ'' 'ፓን አፍሪካን' ሃሳብ በማቀንቀን የ ጋናው ኩዋሚ ንኩማ ከ ንጉሱ ይበልጣሉ::'' በማለት የይበልጣል ያንሳል ሂሳብ ውስጥ ገቡ።በየትኛውም የ ታሪክ መለክያ ግን ''ፓን አፍሪካ'' ማለት ንጉሱ መሆናቸውን እነ ዶክተር ያቆብ ጭምር በ ምርምር ጽሁፋቸውን በማገናዘብ ለ አሜሪካ ሬድዮ ከገለጹ ገና አንድ አመት ያልሞላው ታሪክ ነው።

ይህንን ሁሉ እያሰብን ነው እንግዲህ በ ዓለም በግዙፍነቱ በሚታወቀው የ አሜሪካው ኮንግረስ ላይብረሪ ልዑል ኤርምያስ ሳህለስላሴን ንግ ግር የምናየው።እኛ የ አሁኑ ትውልዶች።እነሆ፦



   ''የይሁዳ አንበሳ ለ ክርስቶስ የተሰጠ ስም ነው።''ልዑል ኤርምያስ ሳህለ ስላሴ


ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ

Regarding copyright I could read from Congress library the following:-
With few exceptions, the Library of Congress does not own copyright in the materials in its collections and does not grant or deny permission to use the content mounted on its website. Responsibility for making an independent legal assessment of an item from the Library’s collections and for securing any necessary permissions rests with persons desiring to use the item. To the greatest extent possible, the Library attempts to provide any known rights information about its collections. Such information can be found in the “Copyright and Other Restrictions” statements on each American Memory online collection homepage. If the image is not part of the American Memory collections, contact the Library custodial division to which the image is credited. Bibliographic records and finding aids available in each custodial division include information that may assist in assessing the copyright status. Search our catalogs through the Library's Online Catalog.

2 comments:

Anonymous said...

Ethiopia endih aynet sew eyalat medrek maggnet alemechalachew yasaznal.

Anonymous said...

ሰላም ጌታቸው ብዙ ብሎጎች አነባለሁ።አስተያየት መስጠት ላይ ግን ሰነፍ ነኝ። ዛሬ ልጎብዝ ነው። ብሎግህን በጣም እከታተላለሁ በተለይ ፖለቲካ ዙርያ ጉዳዮችን የሚያነሱ ብዙ ብሎጎች ለወደፊቱ ምን መሆን አለበት ለሚሉ ወሳኝ ነጥቦች አቅጣጫ አያሳዩም ያንተን የወደድኩት ሰዎች እንዲህ ይሉኛል ሳትል ይበጃል ያልከውን መረጃም ሆነ ዕይታ የሃገሪቱን አንድነት ላይ ባተኮረ መልክ መሰንዘርህ አስደስቶኛል።በፖለቲካውም የበሰለ ሃሳብ ያለህ መስለህ ትታየኛለህ።በርታ።እዚህ ቨርጂንያም ሆነ ሃገር ቤት ብዙ አንባቢዎች እያፈራህ መሆኑን በ ኢ ሜል ሊንክ አድርገው በሚልኩልኝ ብዙ ወዳጆች ተረድቻለሁ።
Thank you again.