ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, May 13, 2012

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመቸውም በባሰ ሁኔታ 'አደጋ' የሚለው ቃል የማይገልጠው አደጋ ላይ ነች።

መግቢያ
«ተዋሕዶ» ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ሲሆን፡ ትርጒሙም «አንድ ሆኖ» ማለት ነው።  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስትያናት ቃሉ  የክርስቶስ ባሕርይ በ«ሰብዓዊ» እና በ«መለኮታዊ» ተለይቶ ሳይሆን መለኮት ከስጋ ጋር ተዋሃደ - አንድ ሆነ  ማለት ነው።
443 ዓ.ም. (451 እ.ኤ.አ.) በሮማ ንጉሥ መርቅያን ዘመነ መንግሥት 650 ኤጲስ ቆጶሳት በተገኙበት የተሰበሰበው የኬልቄዶን ጉባኤ ከሮማው ሊቀ ጳጳሳት ቀዳማዊ ልዮን "ክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት" የሚል ጽሑፍ አቅርቦላቸው ነበር። ዳሩ ግን የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ "ጌታ ሁለት ባሕርያት አሉት" የሚለው ትምሕርት ስሕተት ነው ብሎ ልዮንን አውገዘው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ተለያዩ። የቅዱስ ዲዮስቆሮስን ትምሕርት የሚከተሉ ዛሬአርሜኒያ፣ የሕንደ፣ የግብጽ፣ የሶርያ፤ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ናቸው።
የቤተክርስቲያን መመስረት በኢትዮጵያ የተጀመረው በ ቅዱስ ፊልጶስ መሆኑ ይታወሳል (ሐዋርያት ምዕራፍ 8)፦
«እነሆም፥ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቧም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር...»ሐዋርያት ምዕራፍ 8
በዚህ ንባብ ዘንድ ፊልጶስ ጃንደረባውን  በክርስትና አጠመቀው። ንግሥት ግርማዊት ህንደኬ 7ኛ ከ34 ዓ.ም. እስከ 44 ዓ.ም. ገደማ በኢትዮጵያ የነገሡ ናቸው።
በ4ኛ ምዕተ ዘመን በወንድማማቾቹ ንጉሥ ኤዛና እና ንጉሥ ሳይዛና ዘመን በፍሬምናጦስ አማካይነት ክርስትናየኢትዮጵያ ይፋዊ ሃይማኖት ሆነ። ይህ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ «አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን» ተብሎ ይታወቃል። በወጣትነት ዕድሜው ከአጎቱ ከፈላስፋው ከመሮፔዎስ እና ከወንድሙ ከሲድራኮስ ጋራ መርከባቸው ስለሰመጠች ከወንድሙ ጋር ከሞት ተርፈው ምጽዋ አጠገብ ተገኙ። ወደ ንጉሦቹም ግቢ አመጡዋቸውና ቀስ በቀስ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለበት ደረጃ አገኙ። ንጉስ ኤዛና ደግሞ ወደ ክርስትና ለውጠው እንዲጠመቁ አደረጉ። ኤዛና ፍሬምናጦስን ለኢትዮጵያ አቡነ እንዲሾም ለመጠይቅ ወደ እስክንድርያ ላኩዋቸውና የእስክንድርያ ጳጳስ አትናቴዎስ ፍሬምናጦስን ሾሞ ላከው። ፍሬምናጦስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ሲሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ ደግሞ 111ኛው መሆናቸው ነው።
'አደጋ' የሚለው ቃል የማይገልጠው አደጋ
ባለፈው ሳምንት የተጀመረው በሃገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ እንደተለመደው አሳዛኝ ዜናዎች እየተነበቡበት ጉባዔውን ጀምሯል። ካለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ወዲህ ቅዱስ ሲኖዶስ አግባብነት የሌላቸውን የ ፓትሪያሪኩ ድርጊቶች በ አደባባይ በመኮነን እና ውሳኔ በማሳለፍ ላይ በመሆኑ ከፍተኛ መዋከብ ውስጥ ሆን ተብሎ እንዲገባ እየተደረገ ነው። አሁን ፍንትው ብለው የሚታዩ አደጋዎች ከመቸውም ወቅት በላይ በ ቤተ ክርስቲያን ላይ እያንዣበቡ ነው።
የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን አደጋ መገለጫዎች፣አደጋው በቤተ ክርስቲያን ላይ እና በሃገር ላይ የሚያመጣው መዘዝ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? መፍትሄዎቹስ?

1/ የ ወቅቱ የ ቤተ ክርስቲያን አደጋ መገለጫዎች
  •  ልክ ያጣ ሙስና፣
  • እግዚያብሄርን የማይፈሩ፣ሰውን የማያፍሩ  የ ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር የ ፕትርክናውን ስልጣን ሳይቀር መያዛቸው፣
  • እነኚሁ እግዚያብሄርን የማይፈሩ፣ሰውን የማያፍሩቱ በተለይ ባለፉት ሃያ አመታት የ መንግስት የ ካድሬ ካባ ለብሰው ከ ሹመኞች ጋር በመሞዳሞድ ከስራቸው ሌሎች መሰሎቻቸውን በብዛት ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር( ከ አጥብያ ጀምሮ እስከ መንበረ ዽዽስና ድረስ) ማስረግ መቻላቸው፣
  • የነበረውን የ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ለመበረዝ የተነሱ ጸረ ተዋህዶ ቡድኖች
  • ይህ ቡድን በ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እርስ በርሱ ሲጎራረስ የከረመ ከመሆኑም በላይ በገንዘቡ የማፍያ ቡድን ለማደራጀት ሁሉ የቻለ መሆኑ። ለምሳሌ የመጎራረሱ መታወቂያዎች ለ ፓትሪያሪኩ 'ጥይት የማይበሳው መኪና አጥብያ አብትያተ ክርስቲያናት' ገዙላቸው ብሎ ከመሳለቅ ጀምሮ ከ ሶስት መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ ሃውልት ከ ስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በ ቦሌ ደብረ ሳሌም መድሃኔ ዓለም፣መጥምቀ መለኮት ወ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን እስከመስራት የደረሰ ታላቅ ድፍረት የሚሉት ይጠቀሳሉ።
2/  በዝምታ የተፈታ ችግር የለም!

ላለፉት ሃያ ዓመታት  በ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱት አስነዋሪ አስተዳደራዊ ብልሹነት እና ሃይማኖታዊ መዳፈሮች የሚከተሉትን መዘዞች እንደሚያስከትሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።

መዘዙን ስላላወራነው የማይመጣ መስሎን እጅ እና እግራችንን አመሳቅለን የተቀመጥን ካለን እንደተሳሳትን መረዳት አለብን።አሁን በ ቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው በዝምታ ከታየ ነገ ሊደርስ ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር ኢምንት አይሆንም ብሎ የሚናገር ማን ሊኖር ይችላል?


ቀደም ብሎ በ ሁለት ሲኖዶስ ግራ የተጋባችው  ቤተ ክርስቲያን  ይብሱን በ ሃገር ቤት ያለውን ሲኖዶስ ለ ሁለት በተለያየ መንገድ ለመክፈል (በ አባቶች ጽናት እና በ እግዚያብሄር ቸርነት ከሸፈ እንጂ) በ እየ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔያት ላይ የታየ እውነታ ነው። ይህ ሙከራ ግን ከ አሁን በሁዋላ ገዝፎ እና 'የ እምነት ነጻነት' በሚሉ ሃረጎች ተሸፍነው አስገራሚዎቹ የ ልደታ በታች ፍርድ ቤቶች አይወስኑም ማለት ካለፈው ተሞክሮ አለመማር ብቻ ሳይሆን ቸልተኝነትም ጭምር ነው ሊያሰኝ ይችላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የ ክልል መንግስታት እስኪገነጠሉ መብታቸው ነው ተብሎ በድፍረት በሚነገርባት 'አስደናቂት' ሃገር ውስጥ አይደረግም ብሎ ማለት አይቻልም። 'አንተ እምነትህን ልትጭንበት ነው?' የሚሉ  ቃላት እየተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያንን የመክፈል አዝማሚያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት እና ከመሆኑ በፊት ዛሬ ላይ ሆኖ ተው የሚባለው ተው መባል ያለበት ጊዜ ነገ ሳይሆን አሁን ነው
3/መፍትሄዎቹ በማን እጅ ናቸው?
በሃይማኖት ከ ሚመለከው አምላክ በላይ መፍትሄ ለጋሺም ሆነ ነሺ የለም። ይህ ሁሉንም ያስማማል። እግዚያብሔር ግን የሚሰራበት ሰው ይፈልጋል። ነዳያን የ እለት ጉርስ የ አመት ልብስ እንዲመጸወቱ ያደረገው በ አንዲት ቀን ሃብታም ማድረግ አቅቶት አይደለም።ወይንም የሚሰጠው ጎድሎበት አይደለም። ነገር ግን ለ እኛ መፈተኛ ብሎም መጽደቅያ መንገድ ሲያመቻችልን እንጂ። ስለ እዚህ የ እግዚያብሔር ስራ የመኖሩን ያህል የሰውም ስራ አለ ማለት ነው። አል አዛርን ከሞት ማስነሳት የ አምላክ ስራ የመቃብሩን ድንጋይ ማንሳትና መግነዙን መፍታት የሰው ስራ እንደሆነ ሁሉ።
በ ሊቃነ ዻዻሳት እጅ ያሉ መፍትሔዎች
ከሁሉም በላይ የ እግዚያብሔርን አደራ ተቀብለው  ምዕመኑን የመምራት አደራ የያዙት ሊቃነ ጳዻሳት ወሳኝ እና እጅግ ቁልፍ የሆነ ወቅት ላይ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው። ቤተክርስቲያን ዛሬ የገጠማት ጠላት ከቀደሙት የሚለየው ፊት ለፊት ያፈጠጠ ሳይሆን በ ሰላ አካሂያድ መነሻ እና ግብ አስቀምጦ የሚንቀሳቀስ አውሬ መሆኑ ነው። ለእዚህ ነው ከመስዋዕትነት ያላነሰ ዋጋ መክፈልን መጠበቅ አባቶቻችንን ማዘናጋት የሚሆነው።

ጽድቅና ኩነኔን በሚያምኑ ባለስልጣናት እጅ ያሉ መፍትሔዎች
አንድ ወጣት የ ቤተ ክርስቲያን  ተመራማሪ አንድ ጊዜ ሲናገር ''ኢትዮዽያን ይበልጥ ባወቅናት ቁጥር ይበልጥ የምታንገበግብ ሃገር ናት '' ማለቱን አልዘነጋውም። የ ኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ለ ሃገሪቱ ያለፈ ታሪክም ሆነ አሁን ላለችበት እሷነቷ ፣ክብርዋና ሞገስዋ ወሳኝ ሚና ያላት መሆኑን ተረድታችሁ ለ እውነት የምትቆሙበት፣ በጽድቅ እና ኩነኔ መሃል ያለውን ልዩነት ያህል ያፈጠጠ መሆኑን ልትረዱ ይገባችኋል። በተሳሳተ መንገድ በ ስውር እጃቸውን በ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳረፉ ሁሉ እንዲያነሱ ማገዝ እና በስውር በ አጀንዳነት የተያዙ አጀንዳዎችም ለ ህዝብ ይፋ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል።

በምዕመኑ እጅ ያሉ መፍትሄዎች የ ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን የችግሩ ገፈት ቀማሾች ስለሆኑ የማያውቁት ጓዳ ጎድጓዳ የለም። አሁን በመፍትሄነት እንደዚህ አስቡ ሳይሆን አሁን አድርጉ ማለት ብቻ ነው አስፈላጊው።
ምዕመናን ምን ያድርጉ?
  • በየአጥቢያቸው መፍታት ያሉባቸውን መለስተኛ አለመግባባቶች መፍታት፣
  • የሰንበት ትምህርት ቤቶች በመረጃ፣ በጉልበት፣ ወቅቱ በሚፈልገው ሁሉ ለመገኘት እና ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመታደግ ወስነው መነሳት፣
  • ባለማወቅ የሚያጠፋውን አውቆ ከሚያጠፋው መለየት፣
  • የምግባር ችግር ያለበትን የ ሃይማኖት ችግር ካለበት መለየት እና እንደየችግሩ ስፋት እና ግዝፈት በ ሁሉም አጥቢያዎች ቅራኔዎችን ማምከን፣
  • በመጨረሻም በ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሱ ችግሮችን በ አንድነት እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆኖ መመከት ብሎም ቤተ ክርስቲያንን ለሚመጣው ትውልድ ከ እነ ክብር እና ማዕረጓ ማስተላለፍ
ይቆየን
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ

መግቢያ ማጣቀሻ
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሉሌ መልአኩ፤ ሦስተኛ እትም - ፲፱፻፹፮ ዓ.ም


2 comments:

Anonymous said...

Be ergit sigath kenebarawi huneta bemenesat yimeslegnal. Telat eyasebe yalewn qedmo lemasgenzeb memokerh yibel yemiyasegn new.

Alemayehu of Bole B said...

Getch it is good job, keep it up!

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።